ከወሳኞቹ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጥረት እናደርጋለን-- አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

528

አዲስ አበባ መጋቢት 15/2015 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኮትዲቯር አስተናጋጅነት በሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ከጊኒ ጋር የማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ ማምሻውን ያደርጋል።
በማጣሪያው በምድብ አራት የሚገኙት የሁለቱ አገራት ጨዋታ ከምሽቱ 5 ሰአት ከ30 በሞሮኮ ካዛብላንካ 46 ሺህ ተመልካች በሚያስተናገደው መሐመድ አምስተኛ ስታዲየም ይከናወናል።

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተና አምበሉ ሽመልስ በቀለ ከጨዋታው በፊት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። 

አሰልጣኝ ውበቱ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ተደርጎ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንና የአቋም መፈተሻ ከሩዋንዳ ጋር ማድረጉን አስታውሷል።

“አዳዲስና ነባር ተጫዋቾች በስብስባችን ይዘናል፤ በጉዳት ያጣናቸው ተጫዋቾች ቢኖሩም የተተኩት ተጫዋቾች እያሳዩት ያለው ነገር ጥሩ የሚባል ነው።” ብሏል።

በልምምዱ ተጫዋቾቹ ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆኑ መመልከታቸውን ተናግሯል።

“በምድቡ ቀላል የሚባል ጨዋታ የለም፤ ለሁሉም ቡድን ወሳኝ የሆነ ወቅት ላይ የምንገኝ በመሆኑ ከወሳኞቹ ጨዋታዎች ውጤት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን” ነው ያለው አሰልጣኝ ውበቱ።

የጊኒ ብሔራዊ ቡድን በወጥነት ለረጅም ጊዜያት ጥሩ ነገር እያሳየ መሆኑንና "የምዕራብ እና የሰሜን አፍሪካ ቡድኖችን ስንገጥም ከዚህ ቀደም የነበረንን ሪከርድ ለማሻሻል እየሞከርን ነው።” ብሏል።

በአጠቃላይ የብሔራዊ ቡድኑ ጥሩ መንፈስ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።


 

አሰልጠኝ ውበቱ ከማጥቃት ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄ የአጥቂ ችግር በአንድ ጊዜ የሚፈታ እንዳልሆነና እንደ ቡድን ለመፍታት እየሰሩ መሆኑን ተናግሯል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል ሽመልስ በቀለ በበኩሉ “ስብስቡ ከበፊቱ በተሻለ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና በሞሮኮ የተገኘነው ውጤት ለማግኘት ነው” ሲል ገልጿል።

በአሰልጣኞች ቡድኑና የቡድን አጋሮቹ ሙሉ እምነት እንዳለውና ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ እየተጠባበቁ እንደሚገኝ ተናግሯል።

ሽመልስ በተጋጣሚ ቡድን ውስጥ ስለሚገኘው ናቢ ኬታ ተጠይቆ “ለማንም የተለየ ትኩረት አናደርግም። አንድ ተጫዋች ብቻ ሳይሆን እንደ ቡድን ግብጽን የመሳሰሉ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድኖች ገጥመን አሸንፈናል፤ ከዛሬው ጨዋታም የተሻለ ነገር ለማምጣት ተዘጋጅተናል” ብሏል።

በጨዋታው ላይ በኢትዮጵያ በኩል በሁለት ቢጫ ቅጣት ምክንያት ከሚያመልጠው ምኞት ደበበ ውጪ ሌሎቹ ተጫዋቾቹ ከጉዳትና ቅጣት ነጻ መሆናቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የሁለቱን አገራት ጨዋታ የ35 ዓመቱ ቤኒናዊ ጂንዶ ሆንግናንዳንዴ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

ዋልያዎቹ በሚገኙበት ምድብ አራት ዛሬ ከምሽቱ 4 ሰአት ግብጽ ከማላዊ ጋር በ ‘30 June Stadium’ ጨዋታዋን ታደርጋለች።

ኢትዮጵያ እና ጊኒ ሁለተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን የፊታችን ሰኞ መጋቢት 18/2015 በሞሮኮ መሐመድ አምስተኛ ስታዲየም ያደርጋሉ።

ዋልያዎቹ ከጊኒ ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ወሳኝ ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ አራት ከግብጽ፣ ከማላዊ እና ከጊኒ ጋር የተደለደለ ሲሆን እስካሁን ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች በሶስት ነጥብ እና በአንድ የግብ ክፍያ ምድቡን እየመራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም