ኢትዮ-ቴሌኮም በአዲስ መልክ ያበለጸገውን ቴሌ ብር "ሱፐር አፕ"ይፋ አደረገ 

1516


አዲስ አበባ መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ) ፦ኢትዮ-ቴሌኮም በአዲስ መልክ ያበለጸገውን ቴሌ ብር "ሱፐር አፕ" የሞባይል መተግበሪያ ዛሬ ይፋ አደረገ። 


ተቋሙ የቴሌ-ብር አገልግሎት ባቀረበ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለትራንስፎርሜሽንና የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑ ተገልጿል።


የማህበረሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በማቅለል ረገድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱም እንዲሁ።


በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው መተግበሪያም ከዚህ ቀደም ከነበረው መተግበሪያ ተጨማሪ አገልግሎቶች ተካተውበት በአዲስ መልኩ መበልጸጉ ተገልጿል።


መተግበሪያው ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹና አስተማማኝ መሆኑም ተጠቅሷል። 


የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ኩባንያው አገልግሎቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ መምጣቱን ተናግረዋል።


ኩባንያው ዲጂታል ኢኮኖሚን እውን የማድረግ ሥራን አጠናክሮ በመቀጠል ኢትዮ-ቴሌኮም በዘርፉ የመሪነት ሚናውን እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።


ኃብትን በአግባቡ ለመጠቀም በቴክኖሎጂ መታገዝ ወሳኝ መሆኑን ተናግረው ፤በዛሬው እለት ይፋ የሆነውም መተግበሪያ ይህንን ያሳልጣል ነው ያሉት። 


መተግበሪያው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጥቅም ላይ የሚውሉ መተግበሪያዎች በአንድ የተካተቱበት መሆኑን ገልጸዋል።


ጊዜንና ወጭን በመቆጠብ ረገድ መተግበሪያው ትልቅ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።


አገልግሎቱን ከፕሌይ ስቶር፣ ከአፕ ስቶርና ከአፕ ጋለሪ በማውረድ መጠቀም እንደሚቻል ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም