በግብርና ዘርፍ ሴቶችን ያማከለ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ተደራሽ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ እንደሆነ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ

ባህር ዳር መጋቢት 14/2015(ኢዜአ) በግብርና ዘርፍ ሴቶችን ያማከለ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የኢኮኖሚ አቅማቸውን የሚያጠናክሩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በአማራ ክልል ሰሜን ሜጫ ወረዳ የሴቶችን የግብርና ተሳትፎ የሚያሳይ ጉብኝት ተካሄዷል። 

በጉብኝቱ የተሳተፉት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ እንዳሉት፤ ሴቶች በግብርናው መስክ በተገቢው መንገድ ከታገዙና ከተደገፉ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት የሚላቀቁበት እድል ሰፊ ነው። 

ለዚህም ሴቶችን በግብርና ኤክስቴንሽን ተጠቃሚ በማድረግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የሙያ እገዛ፣ የገበያ ትስስር መፍጠርና ሌሎች ድጋፎችን ሴቶች እንዲያገኙ አሰራር ተቀምጦ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሴቶች ከተደገፉ የተሻለ ለውጥ እንደሚያስመዘግቡ በሰሜን ሜጫ ወረዳ በግብርና መስክ የተሰማሩ ሴቶች ያስመዘገቡት ውጤት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ድጋፉን ማሳደግ ላይ ቀሪ የቤት ስራዎች በትኩረት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል። 

ይህን ለማጠናከር በአማራና ሲዳማ ክልል የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ተቀርፆ መተግበር መጀመሩን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱ ሴቶችን በተለየ ሁኔታ የማብቃትና የማገዝ ስራ እያከናወነ እንደሆነ ጠቁመዋል። 


 

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የስርዓተ ፆታ ባለሙያ ወይዘሮ ማስተዋል ካሳሁን በበኩላቸው በክልሉ ሴቶች በግብርናው ዘርፍ ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በክልል 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚበልጡ ሴቶችን በማካተት የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም በቀበሌ ደረጃ ጭምር ለሴቶች በቅርበት እገዛና ድጋፍ የሚያደርግ ባለሙያ ተመድቦ ሙያዊ እገዛ በመስጠት የግብርና ግብዓትና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የሃብት አጠቃቀምና የስራ ክፍፍል እንዳይኖር ግንዛቤ እንዲያገኙ እየተደረገ ሲሆን በተሰራው ስራም ለውጥ እየመጣ መሆኑን አመልክተዋል።


 

በሰሜን ሜጫ ወረዳ 9 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየተከናወነ ባለው የበጋ ወራት የመስኖ ልማት እንቅስቃሴ 2 ሺህ 500 ሴቶች እየተሳተፉ ነው ያሉት ደግሞ የወረዳው ግብርና ፅህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ እስጢፋኖስ ስሜነህ ናቸው።

ሴቶች የማዳበሪያና ምርጥ ዘር ግብዓት እጥረት እንዳይገጥማቸው በቀበሌ ባለሙያ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በሰሜን ሜጫ ወረዳ እናምርት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ሴት አርሶ አደር መልሽው ሞላ እንዳሉት፤ በግብርና ባለሙያዎች በሚደረግላቸው ድጋፍ ቃሪያ፣ ቆስጣ፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ አቮካዶና ስንዴ እያለሙ ነው።

አሁን ካለሙት ጥቅል ጎመን ብቻ በመጀመሪያ ሽያጭ 13 ሺህ ብር ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ በጠቅላላ ካለሙትም 100 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።

በጉብኝቱ ከፌደራል ግብርና ሚኒስቴርና ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም