የመደመር ትውልድ አቅምን አሰባስቦ አገርንና ዓለምን የመለወጥ ልህቀትን የሚሻና ለስኬቱ የሚተጋ ነው - ዶክተር ምህረት ደበበ

327

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ) የመደመር ትውልድ አቅምን አሰባስቦ አገርንና ዓለምን የመለወጥ ልህቀትን የሚሻና ለስኬቱ የሚተጋ ነው ሲሉ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዶክተር ምህረት ደበበ ተናገሩ።


 

"የመደመር ትውልድ" መጽሐፍ የእንግሊዝኛ ቅጂ የሆነው "Generation Medemer" ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ የማስተዋወቂያ መርሃ-ግብር በወዳጅነት ፓርክ ቁጥር ሁለት እየተካሄደ ነው።


 

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዶክተር ምህረት ደበበ የመደመር ተከታታይ መጻሕፍት የያዟቸውን ፍልስፍናና የለውጥ እሳቤዎች ላይ ዳሰሳ አቅርበዋል።

መደመር እሳቤ መሆኑን ጠቅሰው ጠቅላይ ሚኒስተሩ በመፅሃፋቸው የህይወት ተሞክሯቸውንም እንዳቀረቡ ነው ያነሱት።

መደመር እያንዳንዱን ሃብት እውቀት ጉልበት እሳቤ ጊዜ አሰባስቦ ለለውጥና ለእድገት መጠቀምን ያሳያል ብለዋል።


 

የመደመር ትውልድ ፍቅርና መተባበር፣ ስሜትና አስተውሎት፣ መተማመንን የሚገነባ ማህበራዊ መሠረትን መገንባት፣ ልህቀትን መሻት መገለጫዎቹ ናቸው ብለዋል።

መልካም ሥነ-ምግባር የመደመር ትውልድ ዋነኛ ባህሪ መሆኑን ተናግረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመፅሐፋቸው የመደመር ትውልድ አምስተኛውና  በተዋረዳዊ ቅብብሎሽ የመጣ መሆኑን አብራርተዋል ነው ያሉት።

የዚህ ዓለም ትውልድ በመደመር እሳቤ መተባበርና ያለውን ሁለገብ አቅም ለጋራ ብልፅግና መጠቀም እንዳለበት የሚያትት ነው ብለዋል።


 

ያለንበት ዘመን ሉላዊነት፣ ጂኦ ፖለቲካ፣ ቴክኖሎጂ ያስተሳሰረው በመሆኑ የመደመር ትውልድም ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፋዊነትን የሚያቀነቅን ሊሆን እንደሚገባው መጥቀሳቸውን አትተዋል።

መደመር በአንድነት አገርን ወደ ከፍታ የማሻገር መንገድን የሚያሳይ መነፅር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመደመር እሳቤ ዓለም አቀፋዊ መርሆን ያገናዘበ በመሆኑ ሁሉም የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ እንደየአውዱ ሊጠቀምበት የሚችል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም