የአማራ ክልል ህብረት ስራ ማስፋፊያ ባለስልጣን በክልሉ የሰብል ምርት ዋጋን ለማረጋጋት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

ባህር ዳር መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል እየናረ የመጣውን የሰብል ዋጋ ለማረጋጋት የሰብል ምርት በትስስር ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ህብረት ስራ ማስፋፊያ ባለስልጣን አስታወቀ።

መርከብ ዩኒየን በባህር ዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች 1ሺህ 700 ኩንታል የሰብል ምርት በቅናሽ ዋጋ ማሰራጨት ጀምሯል። 


 

በዚህ ወቅት የባለስልጣኑ ሃላፊ አቶ ጌትነት አማረ እንደገለጹት፤ ህብረት ስራ ማህበራት 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት መድበው የሰብል ምርት በመግዛት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት እየሰሩ ይገኛሉ።

እስካሁን ከ731ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ግዥ መፈፀሙን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ 174ሺህ ኩንታል የሰብል ምርት በትስስር ለገበያ መረጋጋት እንዲውል መደረጉን ገልጸዋል።

እየናረ የመጣውን የሰብል ምርት ዋጋ ለማረጋጋት ትርፍ አምራች በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ ዩኒየኖችና ህብረት ስራ ማህበራት በተመጣጣኝ ዋጋ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ የጋራ መግባባት ተፈጥሮ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ኢብራሂም መሀመድ በበኩላቸው፤ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ገበያው እንዲረጋጋ የሰብል ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ እንዲያቀርቡ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው የመርከብ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ዩኒየን ባሳየው ቁርጠኝነት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጤፍ፣ በቆሎና የዳቦ ዱቄት ማቅረብ መጀመሩ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል። 

ሌሎች ዩኒየኖችና የህብረት ስራ ማህበራትም ይህንን አርአያነት ወስደው በየአካባቢያቸው ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሰብል ምርት በማቅረብ ዋጋውን ማረጋጋት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ፋብሪካዎችም በቂ የስንዴ ምርት እንዲያገኙ ይሰራል ያሉት ዶክተር ኢብራሂም፤ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራትም ምርቱን ለህብረተሰቡ በፍትሃዊነት ተደራሽ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በቀጣይ አንድ ወር ውስጥ 10ሺህ ኩንታል የጤፍ፣ የበቆሎና የዳቦ ዱቄት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን የመርከብ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው እሸቱ አስታውቀዋል።

ለባህር ዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሚሆን አንድ ሺህ 700 ኩንታል ምርት በገበያ ከሚሸጠው ከ600 እስከ 1ሺህ ብር ቅናሽ ማከፋፈል ተጀምሯል ብለዋል።

የልደታ ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ውብርስት እንዳለው፤ ከዩኒየኑ የተረከቡትን 40 ኩንታል የጤፍና የዳቦ ዱቄት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚያሰራጩ ተናግረዋል።

በቀጣይም ማህበሩ በትስስር የሚያገኘውን ምርት በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ነዋሪዎች በፍትሃዊነት በማሰራጨት ገበያው እንዲረጋጋ የድርሻቸውን እንደሚወጣ ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም