ዓለም አቀፉ የቴሌኮምዩኒኬሽን ሕብረት ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚፈልግ ገለጸ

573

አዲስ አበባ መጋቢት 14 /2015 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ የቴሌኮምዩኒኬሽን ሕብረት (አይሲዩ) ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር(ኢመደአ) ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚፈልግ አስታወቀ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ከሕብረቱ የአፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር አን ራቼል ኢን ጋር ተወያይተዋል።


 

ውይይቱ ሁለቱ ተቋማት በጋራ በሚሰሩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ኢመደአ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ያሰፈረው መረጃ ያመለክታል።

አቶ ሰለሞን ሶካ ተቋሙ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ያለማቸውን ምርትና አገልግሎቶች እንዲሁም በኢትዮ ሳይበር ታለንት ልማት ማዕከል የሚገኙ ታዳጊዎች በሳይበር ደህንነት ዘርፎች ያከናወኗቸው ስራዎች አስመልክቶ ለዳይሬክተሯ ገለጻ አድርገዋል።


 

የዓለም አቀፉ የቴሌኮምዩኒኬሽን ሕብረት የአፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር አን ራቼል ኢን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነት በማረጋገጥ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ለመደገፍ እያከናወነ ባለው ተግባር መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ ሁለቱ ተቋማት ተቀናጅተው ውጤታማ ስራዎችን እንዲያከናውኑ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።


 

ሁለቱ ተቋማት የሳይበር ደህንነትን በቅንጅት በማስጠበቅ ረገድ ከአፍሪካ የሳይበር መከላከልና ምላሽ መስጫ (Africa CERT) ጋር እንዲሁም ኢመደአ በተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ጉባኤዎችንና አውደ ርዕዮች ላይ ላይ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ በጋራ እንደሚሰሩ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም