በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምግብና መድሃኒቶችን በመቆጣጠሩ ረገድ የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ ነው - የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን

ሐረር መጋቢት 14/2015(ኢዜአ) በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምግብና መድሃኒቶችን በመቆጣጠሩ ረገድ የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማውን በሐረር ከተማ እያካሄደ ነው።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በግምገማው መድረክ እንደተናገሩት፤ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምግብና መድሃኒቶችን ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።


 

በተለይ ገበያ ላይ ያሉ ምርቶች ትክክለኛ መስፈርት ያላሟሉ፣ የደረጃ ምልክት ያለጠፉ፣ የምርትና አገልግሎት  ማብቂያ ዘመን በውል በማይታወቁ ምርቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ የማስወገድ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም የብቃት ደረጃ ሳይኖራቸው ምርት ባመረቱ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ከመውሰድ ባሻገር በህግ  እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ ማከናወኑን ነው ዋና ዳይሬክተሯ ያመለከቱት።

በተለይ በኮንትሮባንድ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመሆን በርካታ ምግብና መድሃኒት እንዲሁም ሲጋራ በቁጥጥር ሰር መዋላቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ ህገ-ወጥ የምግብና መድሃኒት ንግድ እንዲሁም ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር ቀላቅሎ ለገበያ ማቅረብ አሁንም ፈተና እየሆነ እንደሚገኝና ይህንን ለመቆጣጠር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።በሐረሪ ክልል የምግብና መድሃኒት ቁጥጥርና ጥራት ከማስጠበቅ አንጻር ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ  የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ ገልጸዋል።

ከትንባሆ ቁጥጥር ጋር በተያያዘም ቢሮው ግብረ-ሃይል አቋቁሞ የተቀናጀ የቁጥጥር ስራ እያከናወነ መሆኑንም  ተናግረዋል።

በክልሉ 119 የህክምና መሳሪያና የመድሃኒት ጅምላ አከፋፋይ፣ የመድሃኒት መደብርና ምግብ አምራችና አከፋፋዮች እንደሚገኙም አቶ ያሲን ጠቁመዋል።

ባለስልጣኑ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የግምገማ መድረክ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴራልና የክልሉ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ተቋማት ሃላፊዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም