በኢትዮጵያ የሸማቾችን መብት የሚያስጠብቁ የሸማቾች ማኅበራትን የመደገፍ ሥራ እየተሰራ ነው - የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሸማቾችን መብት የሚያስጠብቁ የሸማቾች ማኅበራትን የመደገፍ ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።  

ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዓለም አቀፉን የሸማቾች መብት ቀን በፓናል ውይይት አክብሯል።

ቀኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ 40 ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ 10 ጊዜ "በደረሰኝ ግብይት ይፈጽሙ፤ መብትዎን ያስከብሩ" በሚል መሪ ኃሳብ ተከብሯል።   

ቀኑ ሸማቹ ያለው መብት ምን ድረስ ነው?፣ ችግር ሲገጥመው መብቱን እንዴት ማስከበር ይችላል? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ዓላማን ያነገበ ነው።  

በውይይቱ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን የሸማቾች መብት የነጋዴው ማኀብረሰብ ግዴታ እንዲሁም ችግሮች ላይ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።     


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ አቶ እንዳለው መኮንን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የሸማቹ መብት ሊከበር የሚችለው ሸማቹ በቅድሚያ ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ ግብይት ሲፈጽም ነው።

"ግብይት በምፈጽምበት ጊዜ መብቴ ተጥሷል የሚል ሸማች ግዥ የፈጸመበትን ደረሰኝ በማቅረብ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይገባዋል" ያሉት ሚኒስትር ደኤታው አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ይህ ሲሆን አይታይም ብለዋል።   

በቅርቡ ከሲሚንቶ ምርት ጋር በተያያዘ ከፋብሪካ የሚወጣበት ዋጋ በመንግሥት የተተመነ ቢሆንም በአግባቡ ተግባራዊ እየሆነ አይደለም፤ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ሸማቹ ሕግን ባለማክበሩ መሆኑን አመልክተዋል።

ያለደረሰኝ ግብይት መፈጸም ሕገ ወጦችን ለመያዝ የሚደረገውን እንቅስቃሴ አዳጋች ከማድረጉም ባለፈ የምርቶችን ደኅንነትና ጥራት ለማረጋገጥ የማያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

ጉዳዩ ለመንግሥት ወይም ለተወሰኑ አካላት ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ዜጋ የመፍትሄ አካል መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።  

መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ማኅበረሰብ አንቂዎች ሸማቾችን ማንቃት ላይ ትኩረት እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።   

ሸማቹ ማኅበረሰብ በሕገ ወጥ ነጋዴዎች የሸማቾች መብት የሚጋፉ ወንጀሎች ሲፈጸሙ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠት እንደሚገባውም ነው ሚኒስትር ደኤታው ያስገነዘቡት።


 

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሸማቾች መብት ጥበቃና ግንዛቤ ዴስክ ሃላፊ ሰይፉ አየለ በበኩላቸው ወንጀሎች የሚሰሩት የት ነው?፣ በሕገ ወጥ መንገድ ክምችት የሚካሄደው የት ነው?፣ የዕቃዎች መከዘኛዎች የት ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ሊመልስ የሚችለው ማኅበረሰቡ መሆኑን አንስተዋል።

"ማኅበረሰቡ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች በሚያጋጥሙት ጊዜ ለፍትህ አካላት የማሳወቅ ልምድ አናሳ ነው" ያሉት ሃላፊው መሰል ችግሮች ካልተፈቱ ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት እንደማይቻል ተናግረዋል።  

የኛ አገር ሸማች የሚንቀሳቀሰው በተናጠል ነው ሲሉ የገለጹት ሃላፊው ለመብቱ የሚታገል ጠንካራ ሸማች ማኅበር አለመኖር ትልቅ ፈተና መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በመሆኑም የሸማቾችን መብት የሚያስጠብቁ የሸማች ማኅበራትን ለማጠናከር የመደገፍ ሥራ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም