የወተት ምርትን ለማሳደግ የዝርያ ማሻሻል፣ የመኖ አቅርቦትና የእንስሳት ማረፊያ ምቹነት ተቀናጅተው መተግበር አለባቸው - የዘርፉ ምሁራን

ሀዋሳ መጋቢት 14/2015(ኢዜአ) የወተት ምርትን ለማሳደግ የዝርያ ማሻሻል፣ የመኖ አቅርቦትና የእንስሳት ማረፊያ ምቹነት ተቀናጅተው መተግበር እንዳለባቸው የዘርፉ ምሁራን አመለከቱ።

የእንስሳት ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዙ ዕቅዶች ስኬታማ እንዲሆኑ መንግስት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የምርምር ማዕከላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመስኩ ምሁራን አስገንዝበዋል።


 

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ በእንስሳት ሀብት ዙሪያ ምርምር እየሰሩ ያሉ ምሁራን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ አቅም በመጠቀም ተጠቃሚ እንድትሆን በስፋት መሰራት አለበት።

በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ስነ-ምግብ ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር አጀቡ ኑርፈታ የእንስሳት መኖ ሲዘጋጅ ምርት ለመስጠት የሚያስችሉ ንጥረ ነገሮችን መያዝ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመሆኑም የእንስሳቱ አመጋገብ ከእንስሳቱ የሚጠበቅን ምርት ሊሰጥ በሚያስችል መልኩ መሆን እንደሚገባው ገልጸው፤ የእንስሳት ዝርያ መረጣና የመኖ አቅርቦት ለውጤታማነት ቁልፍ ጉዳዮች እንደሆኑ ገልጸዋል።

የመኖ ዝግጅት ከመጀመሪያ ጀምሮ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የገለጹት ፕሮፌሰር አጀቡ፤ የአርሶ አደሩን ህይወት ለመቀየርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲም የእንስሳት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ስራ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

በእንስሳትና ተፈጥሮ ግጦሽ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ በእንስሳት እርባታና ጄኔቲክስ ዘርፍ ፕሮፌሰር አበራ መለሰ በበኩላቸው እንዳሉት በዶሮ ስጋና እንቁላል ምርታማነት ላይ በዋናነት የተለያዩ ምርምሮችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የዶሮና እንቁላል ምርታማነትን በማሳደግ እያንዳንዱ ቤተሰብ በአነስተኛ የዶሮ እርባታ ተሳትፎ እንዲኖረው በምርምር የማገዝ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የእንስሳት መኖ ላይ የተደረጉ የምርምር ስራዎች ውጤት እንደታየባቸው አመልክተው፤ ከዶሮ መኖ ጋር በተያያዘ በሞሪንጋ /ሽፈራው/ ተክል ላይ ያደረጉት ምርምር በመኖነት ለዶሮዎች ቢቀርብ የእንቁላል ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚያስችል መረጋገጡን ጠቁመዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር በእንስሳትና ግጦሽ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር፣ ተማራማሪና በወተት ዘርፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ስንታየሁ ይግረም በበኩላቸው በቀን እስከ 30 ሊትር ወተት የመስጠት አቅም ያላቸው ላሞች በአያያዝ ችግር ከስድስት ሊትር በላይ እንዳይሰጡ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ይህን ችግር መፍታት የሚቻለው በተገቢው መንገድ እንስሳቱን መያዝና የተመጣጠነ መኖ በማቅረብ ሲሰራ ነው በማለት ገልጸው፤ ከዝርያ በተጨማሪ የመኖና የእንስሳት ማረፊያ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።


 

የእንስሳትን ምርታማነት የማሳደግ ስራ የዝርያ ማሻሻል፣ የመኖ አቅርቦትና የእንስሳት ማረፊያ ምቹነት ተቀናጅተው መተግበር እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ስንታየሁ፤ በተናጠል የሚካሄደው ስራ ውጤት እንደማያመጣ ገልጸዋል።


 

በመሆኑም ዝርያ ማሻሻል፣ በቂ መኖና ውሀ ማቅረብ፣ እንስሳት ማረፊያ ምቹ ስፍራ ማዘጋጀት ለምርታማነት ማደግ ቁልፍ ጉዳዮች በመሆናቸው ተቀናጅተው መተግበር እንዳለባቸው አስረድተዋል።

እነዚህን ተግባራት በተገቢው መንገድ በመከተል የተሟላ ውጤት ማምጣት የሚያስችል ሙሉ ፓኬጅ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም