የመዲናዋን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍ አሰራሮችን በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል

570

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ኃብት ልማት ቢሮ ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ አሰራሮችን በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ። 

ቢሮው በዘጠኝ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከተገልጋዮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።  

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ኃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ሂክማ ከይረዲን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ተቋማት ከሌብነትና ብልሹ አሰራር በጸዳ መልኩ ለነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል። 

በከተማ አስተዳደሩ ባሉ ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻልና ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት  አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ተደግፈው እንዲከናወኑ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።   

በአገልግሎት አሰጣጣቸው ዛሬ የተገመገሙት ዘጠኙ ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ አስደግፈው ለመስጠት እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል። 

ለአብነትም የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት መረጃ አገልግሎት ኤጂንሲ፣ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲና የእሳት አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ለኅብረተሰቡ ወጪ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋና ከብልሹ አሰራር የጸዳ አገልግሎት ተዳራሽ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል።  

ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራሮችን ለመዘርጋት ለሰራተኞቻቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል። 

በውሃና ፍሳሽ አግልግሎትና በሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት መረጃ አገልግሎት ኤጂንሲ በኩል የሚስተዋሉ የአገልግሎት መቆራረጦች መስተካከል እንዳለባቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች አንስተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም