በከተሞች የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት መንግስት ስትራቴጂክ እቅድ ነድፎ ወደ ስራ ገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
በከተሞች የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት መንግስት ስትራቴጂክ እቅድ ነድፎ ወደ ስራ ገብቷል
ደብረ ብርሃን መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ) በከተሞች የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ባለሀብቶችንና ህብረተሰቡን ያሳተፈ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በኢትዮጵያ የከተሞች ትብብር መድረክ አዘጋጅነት ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሂዷል።
በሚኒስቴሩ የከተማ ቤቶች አቅርቦትና አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፀጋየ ሙሼ እንደገለጹት፤ አሁን ላይ በአገር ደረጃ እየተስተዋለ ያለውን የከተሞችና የገጠር ማዕከላት እድገት የሚመጥን የቤት አቅርቦት እንዲኖር እየተሠራ ነው።
ሚኒስቴሩ በ2013ዓ.ም በ10 ዓመት ውስጥ ሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የከተማ እና የገጠር ቤቶችን በማስገንባት ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ ስትራቴጂክ እቅድ ነድፎ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።
ለመገንባት ከታሰቡት ቤቶች ውስጥም አራት ነጥብ አራት ሚሊዮን የሚሆኑት ቤቶች በተለያዩ ከተሞች የሚገነቡ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በገጠር ማዕከላት የሚገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በከተሞች በሚካሄደው የቤቶች ግንባታ ላይ በመንግስት 20 በመቶ፣ በማህበራት 35 በመቶና ቀሪው 45 በመቶ ደግሞ በባለሀብቶች የሚከናወን መሆኑንም አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር አዳዲስ በሚፈጠሩ የመኖሪያ መንደሮች የውሃ፣ የመብራት፣ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን እንደሚዘረጋ ገልጸዋል።
በዚህም አንዳንድ ከተሞች ለተደራጁ ማህበራትና በሪል ስቴት ግንባታ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ቦታ በማቅረብና ግለሰቦችም ባላቸው ትርፍ ቦታ ላይ ቤቶችን በመገንባት በተመጣጣኝ ዋጋ እያከራዩ እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንዷለም ጤናው በበኩላቸው በተቀናጀ ህዝባዊ ተሳትፎ ከተሞችን በማዘመን ውብ፣ ማራኪና ለኑሮ ምቹ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የከተሞች መድረክ ከተቋቋመ ወዲህ ከተሞች እርስ በእርሳቸው የልምድ ልውውጥ በማድረግ፣ ተሞክሮ በመለዋወጥና አዳዲስ የእድገት አማራጮችን በማፍለቅ ከተሞች እንዲዘምኑ በማድረግ የመጣው ለውጥ ቀላል አለመሆኑን አንስተዋል።
በዛሬው ውይይት ላይ የሚነሱ ነጥቦችን በግብዓትነት በመያዝ በከተሞች እድገት ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥና የሚስተዋሉ ክፍተቶች ላይ በጋራ መክሮ የመፍትሄ ሐሳብ ለማስቀመጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ከተለያዩ የአገሪቷ ከተሞች የመጡ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።