ሐሰተኛ ሰነድ አቅርበሻል በማለት ከአንዲት ግብር ከፋይ 70ሺህ ብር ጉቦ የተቀበለ የገቢዎች ባለሙያ እጅ ከፍንጅ ተያዘ

304

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ)፦ ሐሰተኛ ሰነድ አቅርበሻል በማለት ከአንዲት ግብር ከፋይ ግለሰብ 70ሺህ ብር ጉቦ የተቀበለ የገቢዎች ባለሙያ እጅ ከፍንጅ ተያዘ።

በወንጀሉ ተባባሪ የሆነ አንድ ባለሙያ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የአነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት የአወሳሰን ባለሙያ የአንድ ሠራተኛ የቅርጫፍ ጽህፈት ቤቱ ግብር ከፋይ የሆኑ ግለሰብን ካቀረብሽው 10 ደረሰኞች መካከል 8ቱ የተበላሹ በመሆኑ ወደ አጣሪ ኮሚቴ መላኩን እና ሁለቱ ደግሞ እጄ ላይ ይገኛሉ በማለት ጉዳዩን ለማዳፈን ግን 100ሺህ ብር ጉቦ እንዲሰጠው መጠየቁን ፖሊስ ገልጿል።

የግል ተበዳይ ያቀረቧቸው ሰነዶች ትክክለኛ እንደሆኑ ለማስረዳት ቢሞክሩም ባለሙያው ሳይቀበላቸው መቅረቱንም አክሎ አስታውቋል።

May be an image of money

የአወሳሰን ባለሙያ የሆነው ግለሰቡ በቢሮ ስልክ ደጋግሞ በመደወል የግል ተበዳይን በማስጨነቅ በሕግ እንደሚጠየቁ በማስፈራራት 70ሺህ ብር ለመቀበል መስማማቱንም ፖሊስ ጠቁሟል።

የግል ተበዳይ ጉዳዩን ለተቋሙ ኃላፊዎች በማሳወቅ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የደንበል አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ባደረገው ክትትል በቅርጫፍ ጽህፈት ቤቱ የአወሳሳን ባለሙያ የሆነው ሙያተኛ 22 አካባቢ ከሚገኘው መስቲ ሬስቶራንት አካባቢ መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም ገንዘቡን ሲቀበል እጅ ከፍንጅ መያዙንም አስታውቋል።

የወንጀሉ ተባባሪ የሆነው በተቋሙ የጥቆማ አቀባበል ባለሙያ ከፍተኛ ኦፊሰር የሆነው ሠራተኛ በተመሳሳይ ቀን በጉቦ የተገኘውን ገንዘብ ሲቀበል መገናኛ አካባቢ እንደተያዘ የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመልክቷል።

ማኅበረሰቡ መሰል ወንጀል ፈፃሚዎችን ለሕግ አካላት አጋልጦ የመስጠት ልምዱ ይበል የሚያሰኝ መሆኑንም ገልጿል።

ወደፊትም የሕዝብን እና የመንግሥትን እምነት በማጉደል በማኅበረሰቡ ላይ በደል የሚፈጽሙ አካላትን ወደ ሕግ ለማቅረብ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብሏል ፖሊስ በመረጃው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም