የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ፖሊሲ ቀርጾ የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽ ማድረግ የመንግሥት ትኩረት ነው - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ) የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ፖሊሲ ቀርጾ ለዜጎች የተሟላ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ የመንግሥት የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ አንዱ አካል መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በህፃናት የአመጋገብ ሥርዓት፣ የህፃናት መቀንጨር ያለበትን ደረጃ፣ የሚያጠቡና ነፍሰ-ጡር እናቶች ጤናማ አመጋገብ ላይ ትኩረት ያደረገ የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ስትራቴጂ ዳሰሳ ጥናት ይፋ ሆኗል፡፡


 

በዳሰሳ ጥናቱ መሰረት በኢትዮጵያ የህፃናት ደጋግሞ የመመገብና የተመጣጠነ ምግብ የማግኘት ዕድል ከክልል ክልል የተለያየ ቢሆንም በጥቅሉ ዝቅተኛ  ነው፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ መንግሥት በአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ትኩረት ከሰጣቸው ተግባራት መካከል አንዱ ሥርዓተ-ምግብን ማሻሻል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ምግብና ሥርዓተ-ምግብን ለማረጋገጥ ከምርት እስከ አመጋገብ ባህል ባለው ሂደት በርካታ ተዋንያን የሚሳተፉበት በመሆኑ ተጠያቂነትን ያካተተ የጋራ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅዱ ትልቅ ቦታ የተሰጠው የሰው ኃይል ልማት መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ብቁ የሰው ኃይል ማዘጋጀት የሚቻለው ጤናማ ዜጋ ማፍራት ሲቻል መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር የሥርዓተ-ምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ግልጽ የሆነ ፖሊሲ ማስፈጸም የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ተቀርጸው ትግበራ ላይ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡ 


 

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ እንዳሉት፤ የሕዝቦችን ጤና እና ጤንነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ ምርምሮች ይደረጋሉ፡፡

በእናቶችና ህፃናት የአመጋገብ ሥርዓት ላይ የሚያተኩረው የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ስትራቴጂ የዳሰሳ ጥናትም የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር አቡበከር ካምፖ፤ ኢትዮጵያ የምግብና ሥርዓተ-ምግብን ለማሻሻል የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

ፖሊሲ ከማውጣት ጀምሮ የማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎች፣ ደንቦችና አሰራሮችን ማውጣት የመንግሥትን ቁርጠኝነት ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የምግብ እጥረት ችግርን ለማቃለል እየተደረገ ባለው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ እየታየ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም