ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በቱሪዝም መስክ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በቱሪዝም መስክ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ መጋቢት 14/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በቱሪዝም መስክ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።
ሁለቱ ሀገራት በጋራ ለመሥራት የተስማሙባቸውን ጉዳዮች የሚከታተል የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ማቋቋማቸውም ተገልጿል።
የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢፌዴሪ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሠላማዊት ዳዊት እና የደቡብ አፍሪካ ቱሪዝም ዲፓርትመንት ጄነራል ዳይሬክተር ሚስተር ቪክቶር ታሬጅ ናቸው።
የስምምነቱ ዋነኛ ዓላማ በቱሪዝም እና በኢንቨስትመንት ዘርፍ መረጃ ለመለዋወጥና በዘርፉ ስልጠና በሚሰጥበት አግባብ ላይ ያተኮረ መሆኑን የቱሪዝም ሚንስትሯ አምባሳደር ናኒሴ ጫሊ ገልጸዋል።
ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ከሆኑ ሀገሮች ተርታ በመሰለፏ በጋራ መስራታችን ተጠቃሚ ያደርገናል ሲሉም ተናግረዋል።
ሁለቱ ሀገራት አሁን ያደረጉት ስምምነት የትብብር ግንኙነታቸውን ለማጠናከርና ለጋራ ተጠቃሚነታቸው ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው የደቡብ አፍሪካ ቱሪዝም ዲፓርትመንት ጄነራል ዳይሬክተር ቪክቶር ታሬጅ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዳሏት በማስታወስ።
የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብቶች በተለያዩ መንገዶች በጋራ ለምንሠራቸው ሥራዎች ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉም ብለዋል።
በአዲስ አበባ በዛሬው እለት በተደረገው የስምምነት መርሐ-ግብር የሁለቱ ሀገራት የቱሪዝም ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።