የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ የተፋሰሱን አገራት መተማመን የሚሸረሽር ነው-ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ) ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሚመለከት የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ የመርህ ስምምነቱን የጣሰና የተፋሰሱን አገራት መተማመን የሚሸረሽር መሆኑን የዓባይ ውኃ ጉዳይ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ።

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸውበሚል ግድቡን አስመልክቶ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ የግብጽ መግለጫ ኃላፊነት የጎደለው እና ተቀባይነት የሌለው ሲል ተናግሯል።

መግለጫው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተርና የአፍሪካ ሕብረት የመተዳደሪያ ደንብን የጣሰ ስለመሆኑም አመላክቷል።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን .. 2015 የተፈራረሙትን የመርሆዎች ስምምነት በግልጽ የጣሰ መግለጫ ሆኗል።

በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውኃ ጉዳይ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ፤ በግብጽ በኩል የወጣው መግለጫ የአረብ ሊግን ድጋፍ ለማግኘት ያለመ መሆኑን ይገልጻሉ።

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሚ ሹክሪ፤ የአረብ ሊግ የሕዳሴ ግድብን እንዲቃወምና ከግብጽ ጎን እንዲቆም በማለት በሊጉ ጉባዔ ላይ አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ ሚኒስቴሩሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸውበሚል ሕዳሴ ግድብን በሚመለከት ያወጣው መግለጫ የመርህ ስምምነቱን የጣሰና የተፋሰሱን አገራት መተማመን የሚሸረሽር መሆኑን ፕሮፌሰር ያዕቆብ አብራርተዋል።።

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን የውኃ ሙሌት እያከናወነች ያለው ኃላፊነት በተሞላበትና የታችኞቹን የተፋሰሱ አገራት በማይጎዳ መልኩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ልማቱም የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በግድቡ ዙሪያ በግብጽ በኩል የወጣው መግለጫ ኃላፊነት የጎደለው ቢሆንም ኢትዮጵያ በአስተውሎት ምላሽ መስጠቷን ፕሮፌሰር ያዕቆብ አድንቀዋል።

በኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥረት እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ወደ ኃይል ማመንጨት መሸጋገሩ ይታወቃል።

በመሆኑም በግብጽ መንግሥት በኩል የሚወጡ አደናጋሪ መግለጫዎችን በመተው የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን ሁለንተናዊ ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ነው ያሉት።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት መፍትሔ እንደሚመጣ በማመን የሦስትዮሽ ድርድሩ ሁሉንም አሸናፊ ባደረገ መልኩ እንዲቋጭ አሁንም ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም