የሐጅ ተጓዦች በበይነ-መረብ የሚመዘገቡበት የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሐጅ ተጓዦች በበይነ-መረብ የሚመዘገቡበት የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ
አዲስ አበባ መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ)፦የሐጅ ተጓዦች ለጉዞ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን በማሟላት በየአቅራቢያቸው በሚገኙ የምዝገባ ጣቢያዎች በበይነ-መረብ የሚመዘገቡበት ሥርዓት መዘርጋቱን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ።
የዘንድሮ የሐጅ ጉዞ ተጓዦች 315 ሺህ ብር መክፈል የሚጠበቅባቸው መሆኑንም ጠቅላይ ምክር ቤቱ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ የዘንድሮውን የሐጅ ጉዞ በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም የሃጅ ተጓዦች አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን በማሟላት በየአቅራቢያቸው በሚገኙ የምዝገባ ጣቢያዎች መመዝገብ የሚችሉበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት መዘርጋቱን አስታውቋል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ሸኽ አብዱላዚዝ ሸኽ አብዱል ወሊ፤ በመግለጫቸው 1 ሺህ 444ኛው የሐጅ ጉዞ መስተንግዶን የተቀላጠፈ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
የዘንድሮው የሁጃጆች የጉዞ የመስተንግዶ ሥርዓት ከዚህ ቀደም የነበረውን የጉዞ አገልግሎት በማሻሻል አሰራሩን ግልጽ፣ ቀልጣፋ፣ ተወዳዳሪ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የምዝገባ ሥርዓቱ ከባንክ ክፍያ፣ ከቪዛ፣ ከአየር ቲኬት፣ ከሆቴል አገልግሎት አቅራቢዎችና ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
የሐጅ ተመዝጋቢዎች በተለያዩ ከተሞች የእስልምና ጉዳዮች ቢሮዎች በተዘጋጁ የምዝገባ ጣቢያዎች መመዝገብ የሚችሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ማንኛውም ተመዝጋቢ የታደሰ መታወቂያ፣ ፓስፖርት፣ ጉርድ ፎቶ እና የኮቪድ ክትባት ማስረጃ ማሟላት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የሳዑዲ መንግሥት ክልከላ ያደረገባቸው አካላት መመዝገብ እንደማይችሉ በማስታወቅ ጉዞውንም ለሌላ ዓላማ ለማዋል በማሰብ ምዝገባ ማድረግ እንደማይፈቀድም አሳስበዋል።