የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

616

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የትንበያና የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገለጸ። 

የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ62ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደረጃም ለ42ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ተከብሯል። 

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክንፈ ሃይለማርያም በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ለማኅበረሰቡ ተዳራሽ በማድረግ ደኅንነት ለማስጠበቅና ልማትን ለማፋጠን እየተሰራ ነው።

 ትክክለኛ የአየር ትንበያ መረጃዎች ለጥናት ምርምር ጭምር እንደሚያግዙ ጠቁመው ትክክለኛ የአየር ትንበያ መረጃ እንዲኖር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ጎርፍና ድርቅ ያሉ ክስተቶች በአገሪቷ እየተበራከቱ መሆናቸውን አንስተው እነዚህን ለመቋቋምም የተጠናከረ የአየር ሁኔታ መከታተያ፣ መተንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት በመገንባትና በመዘመን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ለዚህም በሰው ሃብትና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ራሱን በማሻሻል ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

በዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ቢሮ ዳይሬክተር ዶክተር አግነስ ኪጃዚ በበኩላቸው የሚቲዎሮሎጂ  ትንበያ መረጃ በተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመታገዝ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎች የግብርና ሥራዎች ወቅታቸውን ጠብቀው እንዲከናወኑ ከማድረጉም ባለፈ ምርቶች በጊዜ ተሰብስበው ለተፈለገላቸው ዓላማ እንዲውሉ ከማገዝ አንጻር ሰፊ ጠቀሜታ አላቸው። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም