ቀጥታ፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል- የጋምቤላ ክልል

ጋምቤላ መጋቢት 14 /2015(ኢዜአ)፡-  ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፍፃሜውን እስኪያገኝ  ድጋፉን  አጠናክሮ  እንደሚቀጥል የጋምቤላ ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ። 

የህዳሴ ግድብ  12ኛ ዓመትን በማስመልከት በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በመዘዋወር ንቅናቄ እያደረገ ያለው የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ቡድን ዛሬ ጋምቤላ ከተማ ገብቷል።

ለቡድኑ አቀባበል ባደረጉበት ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ ረዳት ፕሮፌሰር ኡቦንግ ኡቻ  እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነት መገለጫ ዓርማ ለሆነው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የክልሉ ህዝብና መንግስት ድጋፍ ሲያደርግ ቆይተዋል።  


 

የግድቡ ግንባታ ፍፃሜውን እስኪያገኝ የክልሉ መንግስትና ህዝብ በቦንድ ግዥ፣ በስጦና ሌሎች ዘርፎች  የጀመሩትን  ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የክልሉ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኮማንደር ጋድቤል ቦል፤ በዘንድሮው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ  ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ቡድኑ ወደ ክልሉ የመጣበት ዓላማ ከግድቡ ግንባታ ጅማሮ አንስቶ የክልሉ ህዝብና መንግሥት እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና ለመቸርና በቀጣይም እገዛውን እንዲያጠናከር ለማበረታታት  መሆኑን የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ቡድን አባል አቶ መኮንን መንገሻ  ገልጸዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን መኩሪያና ለትውልድ የሚተላለፍ ታላቅ የእድገት ተስፋ  ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ማሳያ ግድቡ ያለ ማንም ድጋፍ በኢትዮጵያዊያን የገንዘብና የጉልበት ተሳትፎ   እየተገነባ ያለ መሆኑ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የግድቡ ግንባታ እውን እስኪሆን የህዝቡ ድጋፍና  ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ቡድኑ በጋምቤላ ክልል በሚኖረው ቆይታ በወረዳዎች በመዘዋወር ህዝቡ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና የማቅርብና በቀጣይም ድጋፉን እንዲጠናከር የንቅናቄ ስራዎችን እንደሚያካሄድ ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም