የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሀገር ገፅታ ግንባታና በለውጥ ስራዎች እያከናወናቸው ያለውን ተግባራት አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አዳማ መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሀገር ገፅታ ግንባታና በለውጥ ስራዎች ረገድ እያከናወናቸው ያለውን ተግባራት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ።

የምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን የለውጥ ስራዎች እንቅስቃሴና የአሰራር ማሻሻያዎች ላይ ያተኮረ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ በአዳማ ተካሄዷል።


 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ በዚሁ ወቅት፤ ኢዜአ አበረታች የለውጥ፣ የአሰራርና የይዘት ስራዎች ማሻሻያ እያከናወነ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ የለውጥ ስራዎች "ተቋሙን አሁን ካለበት ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚወስዱ ናቸው" ያሉት ሰብሳቢው፤ በቀጣይም ተወዳዳሪነቱንና ታማኝ የዜና ምንጭነቱን በዘላቂነት ለማስቀጠል በቴክኖሎጂና በሰው ኃብት ልማት ማስደገፍ ይገባዋል ነው ያሉት።


 

ለዚሁ ማጠናከሪያም እየተገበራቸው ያሉትን የሪፎርም ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙን በቀጣይነት ለመደገፍ፣ ለማገዝና ለመከታተል አጋዥ የሆኑ ግብዓቶችና ያለበትን የለውጥ ምዕራፍ የተመለከተ መረጃ ማግኘቱንም ገልጸዋል።


 

ተቋሙ የሁሉም ሚዲያዎች መጋቢና መሪ እንደመሆኑ አሁን ካለበት በላይ ብቁ የሰው ሃይል፣ በቴክኖሎጂና በፋይናንስ አቅም ራሱን ለማጠናከር መስራት እንደሚገባው አመላክተዋል።

በተቋሙ እየተዘጋጀ ያለውን አዲስ የሰራተኞች መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ በግብዓት ለማዳበር የሚያስችል ግንዛቤ መፈጠሩን ጠቅሰዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው መድረኩ ኢዜአ ያለበትን ጉድለት እየፈተሸ ተልእኮውን እንዲያሳካ ገንቢ ግብዓት የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል።

"ኢዜአ ራሱን መመልከት ያለበት ከዓለም አቀፍ አቻ ተቋማት ጋር ነው" ያሉት አቶ ሰይፈ፤ በተለይም በሀገር ገፅታ ግንባታ ላይ የሚጠበቅበትን ሚና መወጣት የሚያስችለውን አቅም ለመፍጠርና ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራ ነው ብለዋል።


 

ተቋሙ ህጎችና አሰራሮችን ከማሻሻል ጀምሮ ዘርፈ ብዙ የለውጥ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሰይፈ፤ በተለይም ተልዕኮውን ለማሳካት የሚያስችለውን አቅም ለመፍጠር ከሀገር ውስጥና ከውጭ አጋር አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በሰው ሃይል አቅም ግንባታና ምቹ የስራ አካባቢ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም