ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች - አምባሳደር ጃኦ ጂዩዋን

314

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2015(ኢዜአ) ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ጃኦ ጂዩዋን ገለጹ። 

በቅርቡ በኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት ልዑክ በቻይና ያደረገው ይፋዊ የስራ ጉብኝት የአገራቱን ግንኙነት በማጠናከር በኩል ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል። 

ልዑኩ በቆይታው ከቻይና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ጋር የሁለቱ አገራት ግንኙነት ሊጠናከር በሚችልባቸው በርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት። 

የንግድና ኢንቨስትመንት፣ የመሰረተ-ልማት ግንባታ ግንኙነቱን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉን ጠቅሰው የብድር ማስተካከያ አስፈላጊነትን በተመለከተም የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በጤና፣ በኃይል ልማትና በማዕድን ዘርፍ ተሳትፏቸው የበለጠ እንዲጠናከር የማበረታታት ሥራው እንደሚቀጥል ማረጋገጫ ተሰጥቷል ብለዋል። 

በተጨማሪም የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ትብብሩን ማሳለጥ የሚያስችል የጋራ ኮሚቴ እንዲዋቀር   ሥምምነት ላይ መደረሱንም አንስተዋል።

እያደገ የመጣውን የሁለቱ አገራት የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከርና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

ዘንድሮ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ለማከናወን ቻይና የቀረጸችው "የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ" 10 ዓመቱን እንደሚይዝ ገልጸው ኢትዮጵያ በእነዚህ ዓመታት ጠንካራ ግንኙነት እንደነበራት አስታውሰዋል።

በቀጣይም በኢኒሼቲቩ ማዕቀፍ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎችን ለማሳለጥና ትበብሩን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል።    

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን አጋርነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው በተለይም የኢትዮጵያ ተማሪዎች በቻይና በዘርፉ የሚሰጣቸውን የሥልጠና እድል ለማስፋት ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

የቻይና ሥመ-ጥር የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ሥራ ተሳትፏቸውን ለማጠናከር እንደሚሰራም ገልጸዋል። 

በሌላ በኩል በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረው ጦርነት በሰላም ሥምምነት መቋጨቱን ቻይና በአድናቆት እንደምትመለከተው ገልጸው ሥምምነቱ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ሰላም ለአፍሪካ ቀንድና ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም ወሳኝ ነው ያሉት አምባሳደር ጃኦ ጂዩዋን ሥምምነቱ ይህንን በማረጋገጥና ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ ሰላምና የአኮኖሚ ግንባታ ሥራ ለመመለስ አበርክቶው ከፍተኛ ነው ብለዋል።  

የኢትዮጵያ መንግሥት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ ቻይና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ትቆማለች ነው ያሉት። 

የመልሶ ግንባታ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ የቻይና ባለሃብቶች በእነዚህ አካባቢዎች በኢንቨስትመንት ሥራ እንዲሰማሩ ለማድረግም ጥረት ይደረጋል ብለዋል። 

ቻይና የዓለምን ሰላም ለማረጋገጥ ባለፈው ዓመት ያወጣችውን "ዓለም አቀፍ የደኅንነት ኢኒሼቲቭ" መሰረት በማድረግ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር በአፍሪካ ቀንድና በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ለማጽናት በቅንጅት እንደምትሰራ ተናግረዋል።

እንደ አወሮፓውያኑ አቆጣጠር 2022 በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ 2 ነጥብ 19 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን በኢትዮጵያ የቻይና ቀጥታ ኢንቨስትመንትም 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። 

የኢትዮጵያና የቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1970 ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም