ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ-መስተዳድር አድርገው ሾሙ

699

አዲስ አበባ መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ-መስተዳድር አድርገው ሾመዋል።

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀፅ 14/2// መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት፤ እንዲሁም በኢፌዴሪ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና ግጭትን ለማቆም በፕሪቶርያ ደቡብ አፍሪካ በተደረገው የሰላም ስምምነት አንቀጽ 10(1) መሠረት አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም በማስፈለጉ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመጋቢት 9/2015 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ደንብን አፅድቋል።

በዚሁ ደንብ አንቀጽ 3(2) መሠረት የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ-መስተዳድር አድርገው ሾመዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎችን ውክልና የሚያረጋገጥ እና አካታች የሆነ አስተዳደር በማዋቀር የክልሉን አስፈፃሚ አካል የመምራት እና የማስተባበር ኃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ህፈት ቤት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም