አገር አቀፍ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት የፊታችን ቅዳሜ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
አገር አቀፍ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት የፊታችን ቅዳሜ ይጀመራል
አዲስ አበባ መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ):- የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበት 12ኛ አመትን ምክንያት በማድረግ አገር አቀፍ የሕዳሴ ግድብ ቦንድ ሳምንት ከነገ በስቲያ በአሶሳ ከተማ ይጀመራል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የግድቡን 12ኛ ዓመት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳሬክተር ፍቅርተ ታምር 12ኛ ዓመቱን አስመልክቶ የተዘጋጁ የገቢ ማሰባሰቢያ እና ሌሎች ሁነቶች ላይ ገለጻ አድርገዋል።
ከሁነቶቹ መካከል ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የሚጀመረው አገር አቀፍ የሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት እንደሚገኝበት ገልጸዋል።
በቦንድ ሳምንቱ 100 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱንም ተናግረዋል።
በተያያዘም መጋቢት 21 ቀን 2015 "ሴቶች እና የሕዳሴ ግድብ" በሚል የሚካሄደውን የፓናል ውይይት ጨምሮ ሌሎች መርሐግብሮች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።
በቦንድ ሳምንቱ የተያዘውን የገቢ እቅድ ለማሳካት የሚመለከታቸው የክልል ተቋማት በትኩረት እንዲሰሩ የጠየቁት ወይዘሮ ፍቅርተ ሕብረተሰቡም ቦንድ በመግዛትና በሌሎች አማራጮች ለግድቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያዊያን አቅም እየተገነባ ለሚገኘው የሕዳሴ ግድብ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ዜጎች በእውቀትና በገንዘብ ያልተቆጠበ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።
በዚህም ከግድቡ ግንባታ መጀመር አንስቶ እስካሁን ከሕብረተሰቡ በቦንድ ሽያጭና በሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰቡን በመግለጫው ተጠቅሷል።
ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ ሕብረተሰቡ ለግድቡ በጉልበቱ አስተዋጽኦ ማድረጉም ተገልጿል።
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ/ም የመሰረተ ድንጋይ መቀመጡ የሚታወስ ነው።