የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ጥረት ይደረጋል- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትምህርት ቢሮ

አሶሳ መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ)- የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ጥረት እንደሚደረግ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡

በክልሉ 2014 የትምህርት ዘመን የተሻለ አፈጻጸም ያመጡ ተማሪዎች የሚሸለሙበትና በቀጣይ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዝ ንቅናቄ መጀመሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ዛሬ በአሶሳ ከተማ በተጀመረው ንቅናቄ ላይ እንደተመለከተው፤ በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል  የሰው ሃይልና በጀትን በአግባቡ ለመጠቀም ጥረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል።


 

በመርሐ ግብሩ ላይ የትምህርት ቢሮ ሐላፊ አቶ ቢኒያም መንገሻ ባደረጉት ንግግር ትምህርት የማኅበረሰቡን ሁለንተናዊ ልማት ማረጋገጥ የሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

12 ክፍል የተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ብዙ ሥራ የሚጠበቅብን መሆኑን በግልጽ ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ትውልድን ማዳን ነው ያሉት ሐላፊው በዘርፉ ያሉ ጎታች አሠራሮችን በማስወገድ  የሰው ሃይልና በጀት በመጠቀም መፍትሔ  ለማምጣት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ጥራት ማሻሻል የሁሉንም ርብርብ የሚሻ በመሆኑ የሚመከከታቸው አካላት ቅንጅታዊ አሠራር ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚያስፈልግ አቶ ቢኒያም አስታውቀዋል፡፡


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ባበክር ሃሊፋ በበኩላቸው 2014 . 12 ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ላይ የተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት በክልሉም ጭምር የትምህርት ጥራት መውረዱን እንዳሳየ ተናግረዋል።

በክልሉ ለተማሪዎች ውጤት መውረድ ምክንያቱ ተደራሽነትን በማስፋፋት ሂደት ጥራትን የማስጠበቅ ሥራ በመዘንጋቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ቆም ብለን እንድናስብ አድርጎናል ብለዋል፡፡

ችግሩን በመፍታት የትምህርት ጥራትን ለመመለስ ሀገር አቀፍ የትምህርት ፍኖተ ካርታን መሠረት በማድረግ ከኅብረተሰቡ ጋር ተከታታይና ጥልቅ ውይይት በማድረግ መፍትሄ ማምጣት ይጠይቃል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት ህዝብን የሳተፈ የትምህርት ጥራት የማሻሻል ሥራ በክልሉ መጀመሩን አመልክተው አመራሩ ግንባር ቀደም ሐላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ባበክር ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በንቅናቄው መርሐ ግብር ላይ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስን ጨምሮ ሌሎችም  የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም