በደቡብ ክልል የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ተገለጸ

456

ሀዋሳ መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ ተከትሎ ጎርፍና ናዳ ይከሰትባቸዋል ተብሎ በተለዩ የስጋት አካባቢዎች የቅድመ መከላከል ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ጋምኣ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ በዝናብ ወቅት የጎርፍና የመሬት ናዳ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ያስከትላል።

በተለይ የወቅቱን የበልግ ዝናብ ተከትሎ በክልሉ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል የስጋት አካባቢዎችን እስከ ቀበሌ ድረስ ባሉ መዋቅሮች በመለየት ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል የውሃ መውረጃ ቦዮችን የመክፈትና ተያያዥነት ያላቸው ተግባራት እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

ለአብነትም በከፍተኛ ሁኔታ የስጋት አካባቢዎች ከሆኑት መካከል ሃላባ ዞን፣ ጉራጌ ዞን (ማረቆና ምስራቅ መስቃን ወረዳዎች)፣ ስልጤ ዞን ቆላማ ወረዳዎች፣ ሀዲያ ዞን ሻሾጎና ብላቴ ተፋሰስ፣ ወላይታ ዞን አበላ አባያ እንደሚገኙበት አመልክተዋል።

በተጨማሪም በጎፋ ዞን ደንባ ጎፋና ሳውላ ከተማ፣ ጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ፣ ደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የስጋት ተጋላጭ ተብለው መለየታቸውን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ለአደጋ እንዳይጋለጡ ማድረግና የውሃ መውረጃ መስመሮች በቆሻሻ እንዳይደፈኑ እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።

የቅድመ መከላከል ሥራዎቹ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በከፍተኛ ንቅናቄ በመሰራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ በሚገኙ ደጋማ ወረዳዎች የመሬት ናዳ የሚከሰትባቸው አካባቢዎች መለየታቸውንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ለአብነትም በጋሞ ዞን ገረሴ፣ ዲታ፣ ጨንቻ፣ ቦንኬ፣ ጋጮ ባባ፣ ዳራማሎና ካምባ ወረዳዎች ከፍታ ቦታዎች በዝናብ ወቅት ለናዳ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በጎፋ ዞን መሎ ኮዛና ገዜ ጎፋ ወረዳዎች፣ ደቡብ ኦሞ ዞን ደቡብና ሰሜን አሪ ወረዳዎች፣ ወላይታ ዞን ኪንዶ ዲዳዬ፣ ካዎና ኪንዶ ኮይሻ ወረዳዎች ነዋሪዎችን በማውጣት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አቶ ጋንታ አብራርተዋል።

የክልሉ መንግስት የጎርፍ አደጋን ስጋት ለመቀነስ በመደበው በጀት ከ90 ኪሎ ሜትር በላይ የውሃ ማፋሰሻ ቦዮች መስራት መጀመሩን ገልጸዋል።

በዚህም አስከፊ ችግሮች የሚከሰትባቸው አካባቢዎችን ከአደጋው መታደግ እንደተቻለ የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የጎርፍና ናዳ አደጋዎች በድንገት የሚመጡ በመሆናቸው አስጊ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ጠቁመዋል።

አቶ ጋንታ አክለውም በተለይም ወራጅ ወንዞች በድንገት በሚጥል ዝናብ ጉዳት እንዳያስከትሉ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።

የበልግ ዝናብ እየተካሄደ ላለው የግብርና ስራ ወሳኝ በመሆኑ ማህበረሰቡ ራሱን ከአደጋ እየተከላከለ ውሃውን በጥንቃቄ ወደ ማሳ በማስገባት ስኬታማ ለመሆን እንዲሰራና የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ እንዲያነሳም መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም