የዓለም ባንክ መንግስት ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት እየወሰደ ላለው እርምጃ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ባንክ መንግስት ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት እየወሰደ ላለው እርምጃ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ
አዲስ አበባ መጋቢት 14/2015 (ኢዜአ)፦ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግስት ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት እያከናወነ ላለው ተግባር ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታወቀ።
የንግድ ስራ ምቹነትን (ኢዝ ዱዊንግ ቢዝነስ) ለማሻሻል እና ምርታማነትን ለማሳደግ ፖሊሲ ተኮር ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም አመልክቷል።
ለስራ ጉብኝት ኢትዮጵያ የሚገኙት የዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ቪክቶሪያ ክዋክዋ ከገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በሁለቱ አካላት የጋራ ፍላጎቶች፣ የልማት ጉዳዮችና ትብብራቸውን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተከሰቱ ተደራራቢ ክስተቶች የፈጠሩትን ተጽእኖ ለመቋቋም ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሚኒስትሩ መንግስት በመልሶ ማቋቋምና መልሶ ግንባታ እንዲሁም የልማት ጥረቶች በተለይም በሰው ሃብት ልማት፣ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ የመሰረተ ልማት ትስስር፣ የኢኮኖሚ ማረጋጋት እና በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ያከናወናቸው ተግባራት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል መንግስት ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳው ይበልጥ ጥልቀት በመስጠት እና የመንግስትን ድርሻ በመመጠን የግሉ ዘርፍ በስራ እድል ፈጠራና ዘላቂ ልማት የተሻለ ቦታ እንዲያገኝ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አቶ አህመድ ገልጸዋል።
የዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ቪክቶሪያ ክዋክዋ በበኩላቸው የኢትዮጵያን በርካታ ክስተቶችን የመቋቋም ጥንካሬና መንግስት የግሉ ዘርፍ መር ልማት ለማምጣት እየወሰደ ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ አድንቀዋል።
የዓለም ባንክ የንግድ ስራ ምቹነትን (ኢዝ ዱዊንግ ቢዝነስ) ለማሻሻል እና ምርታማነትን ለማሳደግ ፖሊሲ ተኮር ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የፋይናንስ ተቋሙ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና ከመንግስት ጋር በመሆን መንግስት ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት እያከናወነ ላለው ተግባር ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የዓለም ባንክ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ቪክቶሪያ ክዋክዋ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ሲያደርጉ እ.አ.አ ሐምሌ ወር 2022 ኃላፊታቸውን ከተረከቡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ጉብኝቱ የዓለም ባንክ “ለረጅም ጊዜ አጋሯ” ኢትዮጵያ ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።