አስፈጻሚው አካል ሀላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ምክር ቤቱ የተጠናከረ ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ ነው---ቋሚ ኮሜቴዎች 

317

ሀዋሳ መጋቢት 13/2015 (ኢዜአ) አስፈጻሚው አካል ሀላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ምክር ቤቱ የቁጥጥርና ክትትል ሥራ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ገለጹ።

ሰብሳቢዎቹ በምክር ቤቱ የሚወጡ ህጎች፣ አዋጆችና ደንቦች በትክክል ሥራ ላይ መዋላቸውን በመገምገም ክፍተት ሲኖርም ፈጥኖ እንዲታረም የማድረግ ሥራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች እንዲታረሙ ትኩረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በሲዳማ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አየለች ሌዳሞ እንዳሉት፣ አስፈጻሚው አካል የተጣለበትን ሀላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ኮሚቴው አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል።

"በእዚህም ቋሚ ኮሚቴው የሚከናወኑ ጉዳዮችን በመገምገም ያሉትን ጥንካሬዎችና ጉድለቶች ለይቶ ግብረ መልስ ይሰጣል" ያሉት ሰብሳቢዋ፣ በተሰጠው ግብረ መልስ መሰረት ጉድለቶች መታረማቸውን ክትትል እንደሚደረገም አስታውቀዋል።

በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ከመከላከል አንጻር ለሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት ተገቢ ድጋፍ በማድረግ ጥቃቶችን ቀድሞ ከማስቆም አንጻር ጥሩ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከሴቶች ተጠቃሚነት አንጻር በክልሉ ጥሩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን በተደረገው ክትትል መረጋገጡን የገለጹት ወይዘሮ አየለች፣ "በአሰራር የገጠሙ ጉድለቶች እንዲታረሙ በቋሚ ኮሚቴው በኩል በቂ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው" ብለዋል።

ሰብሳቢዋ እንዳሉት ከአገልግሎት አሰጣጥና ሙስና ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመገምገምና አስተያየት በመስጠት የህዝቡ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝም በትኩረት እየተሰራ ነው።

በምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ዮሳ በበኩላቸው እንዳሉት የምክር ቤቱ አባላትና ቋሚ ኮሚቴው አስፈጻሚውን አካል ከመከታተል፣ ከመቆጣጠርና ከመደገፍ በተጨማሪ የወጡ ህጎች በአግባቡ ሥራ ላይ መዋላቸውን ይከታተላሉ።

በክልሉ ምክር ቤት የተለያዩ አዋጆች እንደሚወጡ ያስታወሱት አቶ ዮሴፍ "ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በትክክል ሥራ ላይ ውለው ያመጡትን ለውጥ ክትትል ይደረጋል" ብለዋል።  

በዚህ በኩል በክልሉ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ መልካም የሚባል መሆኑን ገልጸው፣ ኮሚቴው  የተሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ያደረጋቸው የክትትል ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን አብራርተዋል።  

ትልቅ ስጋት እየሆነ የመጣውን ሙስናና ብልሹ አሰራር ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የምክር ቤቱ አባላት ሚናቸው የላቀ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልል ጥያቄን ተከትሎ በነበረው የሽግግር ጊዜ ግርግሩን ተጠቅሞ የተሰሩ የሙስና ወንጀሎች እንዳሉ የተናገሩት አቶ ዮሴፍ፣ ይህን በተገቢው መንገድ ተከታትሎ ለማረምና የተመዘበረ ሀብት ለማስመለስ ምክር ቤቱ በትኩረት መስራቱንም አመልክተዋል።

በእዚህም ባለፉት ሰባት ወራት ከምዝበራ ጋር በተያያዘ በተደረገ የኦዲት ግኝት 21 ሚሊዮን ብር ተመላሽ መደረጉንም አቶ ዮሴፍ ገልጸዋል።

"ከዚህ ባለፈ 100 የሚሆኑ አመራሮች፣ የስራ ሀላፊዎች እና ሠራተኞች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል" ብለዋል።

የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚጎዱ ተግባራት ተጠያቂነት ባሰፈነ መልኩ በአግባቡ እንዲታረሙ ምክር ቤቱ የሚያደርገው ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር ሁለተኛ የስራ ዘመን አራተኛ መደበኛ ጉባዔ በሃዋሳ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም