ባለፉት ሰባት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቅመማ ቅመም ምርት 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ሰባት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቅመማ ቅመም ምርት 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ መጋቢት 13/2015 (ኢዜአ) ባለፉት ሰባት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቅመማ ቅመም ምርት 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር፤ ኢትዮጵያ ከቅመማ ቅመሞች የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ አዳዲስ ቅመማ ቅመሞችን ጭምር ወደ ተለያዩ ዓለም ሀገራት እየላከች መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ባለፋት ሰባት ወራት 3 ሺህ 374 ቶን ቅመማ ቅመሞችን ወደ ተለያዩ ዓለም ሀገራት በመላክ ከ7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል።
ከዚህም ውስጥ 3 ሚሊዮን 241 ዶላሩ የተገኘው በዘንድሮው ዓመት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጭ ከላከቻቸው ምርቶች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቅመማ ቅመም ምርቶቹ ወደ ህንድ፣ሱዳን፣ኢንዶኖዥያ፣ግብጽ ፣ሳውዳረቢያ እና አሜሪካ ተልከው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘታቸውን ተናግረዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ኢትዮጵያ እስካሁን ወደ ውጭ ሀገራት ልካ የማታውቃቸው አዳዲስ ቅመሞችን ወደ ተለያዩ ዓለም ሀገራት መላክ ጀምራለች ።
በዚህም ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ሮዝመሪ፣አሪቲ እና ጦስኝ ያሉ ቅመማ ቅመሞችን ወደ ተለያዩ ዓለም ሀገራት በመላክ ከቅመማ ቅመሞች የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከቡና ቀጥሎ ያላትን የቅመማ ቅመሞች ጸጋዎች በመጠቀም ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝቷን እንድታሳድግ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ሰለመሆኑ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በ2014 በጀት ዓመት 6 ሺህ 401 ቶን ቅመማ ቅመም ወደ ውጪ በመላክ 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሏን ከኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።