የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕወሓት ላይ አሳልፎ የነበረውን የሽብርተኝነት ውሳኔ አነሳ

469

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2015 (ኢዜአ)፦  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ላይ አሳልፎ የነበረውን የሽብርተኝነት ውሳኔ አነሳ።  

የሕወሓት ከአሸባሪነት መነሳት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በፌደራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰውን የሠላም ሥምምነት ተግባራዊነት ለማፋጠን ይረዳልም ተብሏል። 

በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ ሕወሓት ከአሸባሪነት መዝገብ እንዲነሳ ያስፈለገበትን ምክንያት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በአገሪቷ ዘላቂ ሰላም እየሰፈነ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ይህም ለኢትዮጵያ ህዝብ እፎይታ የሰጠ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ህወሓት ሲከተለው ከነበረው  ኢህገ-መንግስታዊ   እና በሽብር እንዲፈረጅ ያደረጉትን ተግባራት እያሻሻለ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡


 

በሰላም ስምምነቱ ወቅት መግባባት ላይ የተደረሱባቸው ነጥቦችም ፍሬ ማፍራት መጀመራቸውን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ በልጂጌ፤ ስምምነቱን በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም በሕወሓት ላይ አሳልፎ የነበረውን የአሸባሪነት ውሳኔ እንዲያነሳ ጠይቀዋል፡፡ 

ይህም  እንደ አገር ዘላቂ ሰላምን ለመገንባትና ልዩነቶችን በሰለጠነ መልኩ ለመፍታት አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ምክር ቤቱም ከዚህ ቀደም አሳልፎት የነበረውን የአሸባሪነት ውሳኔ በማንሳት የሰላም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲደረግ የበኩሉን እንዲወጣ የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የምክር ቤቱ አባላት፤ ኢትዮጵያ ወደ ዘላቂ ሰላም እንድታመራ ከዚህ ቀደም ተላልፎ የነበረው ውሳኔ መነሳቱ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ 

ይህም የሰላም ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግና የተጀመረውን የሰላም ሂደት ለማጽናት ያግዛል ነው ያሉት፡፡ 

የውሳኔ ሃሳቡን በመቃወም አስተያየታቸውን የሰጡ የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው በሰላም ስምምነቱ መሰረት ሕወሓት ትጥቅ ባልፈታበት ሁኔታ ከአሸባሪነት መዝገብ ማንሳት በአገር ላይ አደጋ ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ 

ሕወሃት ከአሸባሪነት መዝገብ ከመነሳቱ በፊት የሰላም ስምምነቱ አተገባባር ለምክር ቤቱ ቀርቦ መገምገም እንዳለበት አንስተው፤ የውሳኔ ሃሳቡን ተቃውመዋል፡፡


 

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄና አስተያየቶች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በምላሻቸውም ህወሃትን ከአሸባሪነት መዝገብ ማንሳት የሰላም ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም፣ ስምምነቱን ሳይሸራረፍ ተግባራዊ ለማድረግ እና የተጀመረውን የሰላም ሂደት ለማጽናት ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል። 

በሰላም ስምምነቱ መሰረት የሕወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት ሂደት ከከባድ መሳሪያዎች መጀመሩን ጠቅሰው፤ ሕወሃትን ከአሸባሪነት መዝገብ ማንሳት ይህን ስራ ለማጠናከር እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

በመሆኑም የምክር ቤቱ አባላት የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ እንዲያጸድቁ ጠይቀዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ጥልቅ ውይይት ካደረጉ በኋላ በአብላጫ ድምጽ አጽድቀዋል፡፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም