የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በደብረ ብርሀን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በደብረ ብርሀን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ ድጋፍ አደረገ
ደብረ ብርሃን መጋቢት 13/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በደብረ ብርሀን ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚውል ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ ድጋፍ አደረገ።
በማህበሩ የሰሜን ሸዋ ዞን ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዳምጠው እምሻው ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት ማህበሩ ለተፈናቀሉና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ተከታታይ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ዛሬ የተደረገው ድጋፍም ለ2 ሺህ 500 ቤተሰቦች የሚሆን 350 ኩንታል የዳቦ ዱቄትና 1 ሺህ 225 ሊትር የምግብ ዘይት መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህ ተፈናቃዮች የእለት ምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ መጠለያና ሌሎች ድጋፎችን በቀጣይነት እንዲያገኙ ለማስቻል የማህበሩ ደጋፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ የተፈናቃዮች አስተባባሪ አቶ አንተነህ ገብረ እግዚአብሄር እንደገለጹት እስካሁን መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ምግብ፣ አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አውስተዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም ካለው ተፈናቃይ ብዛት አንጻር ድጋፉ በቂ አለመሆኑን ጠቁመው ሁሉም አካል ትብብሩን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የመጠለያ ጥበቱን ለመቅረፍም ከተለያዩ ረጅ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተጨማሪ ጊዜያዊ መጠለያ በማስገንባት ላይ መሆኑን ገልጸው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ድጋፉን ካገኙት መካከል ወይዘሮ አለሚቱ መርጊያ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ከችግሩ በዘላቂነት ለመውጣት ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለስ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
ሌላው የድጋፉ ተጠቃሚ አቶ መሀመድ ይብሬም እንዲሁ ካሉበት ችግር አንጻር ድጋፉ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።