ቀጥታ፡

የረመዳን ወር በጎ ተግባራትን የሚከወንበት በመሆኑ የተቸገሩ ወገኖች በመደገፍ ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል - የእምነቱ ተከታዮች

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2015(ኢዜአ)፦የረመዳን ወር በጎ ተግባራትን የሚከወንበት በመሆኑ የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍና በመርዳት ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል ሲሉ የእምነቱ  ተከታዮች ተናገሩ።  

የ1444ኛው ዓመተ ሒጅራ የረመዳን ጾም በነገው ዕለት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገልጿል።

የረመዳን ወር የምህረት ወር፣ የመስጠት፣ የአብሮነት ብሎም ሰው ከቂምናጥላቻ በመላቀቅ ከፈጣሪ ጋር የሚቀርብበት ልዩ ወር መሆኑን የእምነቱ አስተምህሮ ይገልጻል።

በዚህ በጎ ተግባራትን በሚከወንበት ወር የተቸገሩ ወገኖች በመደገፍና በመረዳዳት ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል ሲሉ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የእምነቱ ተከታዮች ተናግረዋል። 

ከአስተያየት ስጪዎቹ መካካከል አቶ አብድረዛቅ ፈለቀና ወይዘሮ አሚና ሸሪፍ በዚህ ወር ሁሉም ካለው ላይ በመቀነስ ለሌላው በማካፈል የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመንከባከብ ለወገኖቹ አጋርነቱን ማሳየት አለበት ብለዋል። 

እነርሱም በዚህ የረመዳን ወር ያላቸውን በማካፈል፣ የተቸገሩት  በመደገፍና በመንከባከብ ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል። 

በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ላይ የወደቁ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የመደገፍና የማገዝ ሥራ በመሥራት የበኩላችንን ለማድረግ ተዘጋጅተናል ያሉት ደግሞ አቶ ኑርዬ ሀጂመሐመድ ናቸው።

ወይዘሮ አሚና ሸሪፍም ማኅበረሰቡ እርስ በእርሱ በመረዳዳት ይህን ወቅት ማለፈ እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ጾሙ ለመላው ሙስሊም ማኅበረሰብ የአንድነት፣ በጎ ነገር የማድረግ፣ የመተዛዘንና የበረከት እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም