የመደመር እሳቤ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ጎዳና ለማራመድ ግልጽ እሳቤ ብቻ ሳይሆን ተግባር ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

153

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2015 (ኢዜአ)፦ "የመደመር እሳቤ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ጎዳና ለማራመድ የሚያስችል ግልጽ እሳቤ ብቻ ሳይሆን ተግባር ነው" ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት ትናንት ማምሻውን በተካሄደው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ 'የመደመር ትውልድ' መጽሐፍን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የማስተዋወቂያ መድረክ ላይ ነው።

ባለፉት አምስት ዓመታት በመደመር ላይ ያጠነጠኑ ሶስት መጻህፍትን በመጻፍ የመንግስት እና የፓርቲውን ጉዞ በግልጽ ሀሳብ ማሳየታቸውን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

የ'መደመር' እና 'የመደመር መንገድ' መጽሐፍት ሽያጭ ገቢ ለትምህርት ቤቶች ግንባታ መዋሉን አስታውሰው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ 'የመደመር ትውልድ' መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ ደግሞ ለቱሪስት መዳረሻ ልማት እንዲውል ለክልሎች በማበርከታቸው አመስግነዋል።

'የመደመር እሳቤ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የሚወስድ እሳቤ ብቻ ሳይሆን ተግባር ነው' ያሉት አቶ ሽመልስ፤ በመደመር እሳቤ በእርዳታ ላይ የተመሰረቱ አካባቢዎችን በጋራ በማልማት የዜጎችን ሕይወት መለወጥ ተችሏል ብለዋል።

መደመር ተቃርኖዎችን የሚያስታርቅ እሳቤ መሆኑን ተናግረዋል።

የጠራ አስተሳስብ እና አስተሳሰቡን የሚፈጽም ትውልድ በመኖሩ የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ያረጋግጣል ነው ያሉት። 

በተያያዘም በመርሐግብሩ ባለሀብቶች 'የመደመር ትውልድ' መጽሐፍን በመግዛት ለሶፍዑመር ዋሻ ልማት ያሳዩትን አጋርነት አድንቀዋል።

ሶፍዑመር ዋሻ ሸኸ ሶፍዑመር በተለያዩ ቋንቋዎች ቁራን ሲያስተምሩበት የነበረ ታሪካዊ ሥፍራ መሆኑን አስታውሰው፤ ቦታውን ለቱሪስት መዳረሻ ምቹ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጥቂት ዓመታት ውስጥ ባለ አምስት ኮከብ ሪዞርትን ጨምሮ የቱሪስቶች መዳረሻ መሰረተ-ልማት ተገንብቶ እውን እንደሚደረግም አረጋግጠዋል። 

ኢዜአ ያነጋገራቸው ባለሀብቶች አቶ አብዲሳ ሚዴቅሳ እና አቶ ኑር ሁሴን ሶፍዑመር ታሪካዊ ስፍራ በመሆኑ፤ ቦታው የጎብኝዎች መዳረሻ በመሆን የውጭ ምንዛሬ ገቢ የማስገኘት ትልቅ አገራዊ አቅም እንዳለው ገልጸዋል።

ባለሀብቶቹ 'የመደመር ትውልድ' መጽሐፍን ከመግዛት ባለፈ በሶፍ ዑመር ዋሻ ልማት የቴክኒካል እና ገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም