ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት አገርን ለመገንባት  ለጸረ ሙስና ትግሉ ውጤታማነት ሁሉም  ኃላፊነቱን  ሊወጣ ይገባል

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2015 (ኢዜአ) ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት አገርን ለመገንባት  ለጸረ ሙስና ትግሉ ውጤታማነት ሁሉም  ኃላፊነቱን እንዲወጣ የፌደራል ሥነምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

ኮሚሽኑ በፌዴራል ተቋማት ስር ለሚገኙ ለስነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ክፍል፣ ለውስጥ ኦዲት አገልግሎት፣ለሕግ አገልግሎት እና ለተቋማት ለውጥ ስራ አመራር  ኃላፊዎች ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ በቢሾፍቱ ተጀምራል።

በስልጠናው የዩኒቨርስቲዎች ሥነምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ክፍል ኃላፊዎችም ተሳትፈዋል።

የፌደራል ሥነምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ ሙስና ኢትዮጵያ ከተጋረጡባት ዋንኛ  ችግሮች መካከል አንዱ መሆኑንና እየቀያየረ ያለው ሙስና የኢኮኖሚ እድገትን በመግታት ፣አንድነትን በማናጋት ስርዓተ መንግስቱን ለመናድ አደጋ የሚጋርጥ መሆኑን ገልጸዋል ።

ችግሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የደህንነት ስጋት በመሆኑ መንግስት ሙስናን ለመታገል ብሔራዊ ኮሚቴ አዋቅሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ጠንካራ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት አገር ለመገንባት የተጀመረው የፀረ-ሙስና ትግል ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን  ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሁሉም የፀረ-ሙስና ትግሉ ባለቤት መሆን እንዳለበትም ነው ምክትል ኮሚሽነሩ ያመለከቱት።

ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ከ260 በላይ የፌደራል ተቋማት የስራ ኃላፊዎች መሳተፋቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም