የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕወሓት ላይ አሳልፎ የነበረውን የሸብርተኝነት ውሳኔ አነሳ

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2015 (ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ላይ አሳልፎ የነበረውን የሸብርተኝነት ውሳኔ አነሳ።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ ለምክር ቤቱ ሕወሓት ከሽብርተኝነት ስያሜ እንዲነሳ የመንግሥትን አቋም አቅርበዋል።

ምክር ቤቱም በቀረበው ጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ በአብላጫ ድምጽ ሕወሓት ከሽብርተኝነት ስያሜ እንዲነሳ ወስኗል።

ሕወሓት ከአሸባሪነት መነሳቱ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በፌደራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰውን የሠላም ሥምምነት ተግባራዊነት ለማፋጠን ይረዳል ተብሏል።

ያም ብቻ ሳይሆን የሠላም ሥምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግና የተጀመረው ሰላም ሂደትን ለማጽናት እንደሚያግዝ እንዲሁም በክልሉም ሰላም ለማረጋገጥ አስተዋጽዖ የጎላ መሆኑ ተጠቁሟል።

ለአገሪቱም ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትም ሕወሓት ከሽብርተኝነት ስያሜ መነሳቱ ሚናው የጎላ መሆኑን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም