በአገር አቀፍ ደረጃ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮችን በማደራጀት ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም እርሻ እየለማ ነው - የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት 

127

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2015 (ኢዜአ):- በአገር አቀፍ ደረጃ  አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች በማደራጀት ስድስት ሚሊዮን ሄክታር  መሬት በኩታ ገጠም እርሻ  እየለማ መሆኑን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያን የግብርና መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት አቅዶ እየሰራ ይገኛል።

መዋቅራዊ ሽግግሩን በማሳካት ሂደት የኩታ ገጠም እርሻ አንዱ ተግባር መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ለኢዜአ ገልጸዋል።

"የኢትዮጵያ 90 በመቶ አርሶ አደሮች አነስተኛ የማሳ ይዞታ ያላቸውና ኋላ ቀር እርሻ የሚከተሉ፣ የሚያመርቱትም ምርት ከራሳቸው ፍጆታ ያለፈ ባለመሆኑ ዘርፉ መዋቅራዊ ሽግግር የግድ ያስፈልገዋል"  ብለዋል።

ለዚህም አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም እርሻ በማደራጀት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም አገራዊ ለውጡን ተከትሎ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም እርሻ በ85 ሺህ ክላስተሮች መደራጀቱን አመልክተዋል።

በእነዚህ ባለ አነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች የሚለማው የኩታ ገጠም እርሻም ስድስት ሚሊዮን ሄክታር የደረሰ ሲሆን አርሶ አደሮችም በገበያ ተኮር የግብርና ልማት እየተሳተፉ መሆኑን ነው ዶክተር ማንደፍሮ የገለጹት።

በክላስተር የተደራጁ አርሶ አደሮች የእርሻ ሜካናይዜሸን፣ የአንድ መስኮት አገልግሎት፣ ዘመናዊ የግብዓት አቅርቦት እንዲሁም በምርት ግብይት ሰንሰለት ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዚህም በኩታገጠም እርሻ የተደራጁ አርሶ አደሮች  ሁሉም የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጣቸውን ገልጸው፤  ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ገበያ ማቅረብ የጀመሩ አርሶ አደሮች መፈጠራቸውንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የኩታ ገጠም እርሻንና የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት ኢንስቲትዩቱ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የሜካናይዜሸን አገልግሎት ጣቢያዎችም በየአካባቢው በመቋቋም ላይ ናቸው ብለዋል።

የአገልግሎት ጣቢያዎችም የእርሻ፣ የማጨጃና የመውቂያ መሳሪያዎችን የማከራየት፣ አርሶ አደሮችን የማሰልጠን፣ የእርሻ መሳሪያዎችን የመጠገን ስራን በአርሶ አደሩ አቅራቢያ ሆነው እየሰሩ መሆኑን ነው ያብራሩት።

የግብአት አቅርቦትንም በአንድ መስኮት አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን  እስካሁንም 14 የዘር ማበጠሪያ፣ ማሸጊያና ማከፋፈያ ማዕከላት መቋቋማቸውን አመልክተዋል።

በኩታ ገጠም የተደራጁ አርሶ አደሮችም የማዳበሪያና የኬሚካል ግብዓቶችን በቅርበት የሚያገኙባቸው 280 ሱቆች መከፈታቸውን አክለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም