የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ለወጣት ስራ ፈጣሪዎች የፋይናንስ እገዛ እንዲደረግ ጠየቀ

234

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2015 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ለወጣት ስራ ፈጣሪዎች ፖሊሲን መሰረት ያደረገ የፋይናንስ እገዛ እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ አዳዲስ ሃሳብ ይዘው የሚመጡ ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን የሚያስተናግድ የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማኅበር ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ''ዘለላ'' የተሰኘውን የትስስርና የፖሊሲ አድቮኬሲ የውይይት መድረክ አካሄዷል።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ሳሚያ አብዱልቃድር፤ በርካታ የፈጠራ ባለቤቶች የፋይናንስና መሰል ድጋፎችን ባለማግኘታቸው ያሰቡትን ለማሳካት እየተቸገሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሩን ለመፍታት የፋይናንስ ስርዓቱን አካታች በማድረግ ለወጣት ስራ ፈጣሪዎች በፖሊሲ የተደገፈ የፋይናንስ እገዛ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በተያያዘም ማህበሩ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ለመስራትና መፍትሔ ለማፈላለግ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አመልክተዋል።

በዚህም ከአንድ ሺህ በላይ አባላትን በማሰባሰብ ከ17 በላይ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ትስስር እንዲፈጠርላቸው ማድረጉን ነው ፕሬዝዳንቷ የጠቆሙት።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ስራ ፈጣሪዎችም በመንግስት በኩል የፋይናንስና የስልጠና ድጋፍ ቢሟላ አገር የሚጠቅም ስራ ማከናወን እንደሚችሉ ተናግረዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽን ስታርት አፕ ልማት ሊድ ስራ አመራር  ሰላምይሁን አደፍርስ በበኩላቸው የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ዜጎች የሚደግፍ የፋይናንስ ፖሊሲ አለመኖሩ ችግር ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አዳዲስ ሃሳብ ይዘው የሚመጡ ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን የሚያስተናግድ የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርብ ጊዜ ስራ ላይ ይውላል ብለዋል።


 

የፖሊሲ አድቮኬሲ ውይይት ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አመራሮች፣  የባንኮች ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።

በወር አንድ ጊዜ የሚካሄደው ውይይት በቴክኖሎጂ ዘርፍ የፈጠራ ብቃት ያላቸው ወጣቶች ከመንግስትና ከግሉ ዘርፍ የፋይናንስ ድጋፍና ስልጠናዎችን በሚያገኙባቸው መስኮች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም