የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን የግል ባለኃብቱ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል -የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን የግል ባለኃብቱ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል አመለከቱ። 

በአምራች ዘርፉ የተሰማሩ ከ350 በላይ ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከሚያዚያ 28 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ትናንት ምሽት በተዘጋጀ መርሃ ግብር ይፋ ተደርጓል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር  ዶክተር ዓለሙ ስሜ፣ባለኃብቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።   

የኤክስፖው ዋነኛ ዓላማው በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተመረቱ ምርቶች፣የተገኙ ውጤቶችን በአገር፣አህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ መሆኑም ነው የተገለጸው።

የአምራቾችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከር፣ልምድ እንዲለዋወጡ ማስቻል እና የገበያ ዕድሎችን መፍጠርም እንዲሁ። 

በኤክስፖው ላይ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ በአምራች ዘርፉ የሚሳተፉ 350 ድርጅቶች ምርቶታቸውን ይዘው እንደሚቀርቡ ታውቋል።   

300 ሺህ የሚጠጉ ጎብኚዎች በኤክስፖው ላይ እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን የፌደራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣የፋይናንስ ተቋማት፣የንግድ ማኀበራት፣ላኪዎች እና ባለኃብቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።   

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ በዚሁ ጊዜ ፤በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካኝነት የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡    

ንቅናቄው ከውጭ የሚገባውን ምርት በመተካት እና የውጭ ምንዛሬ ግኝት በማሻሻል ረገድ አበረታች ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡   

ንቅናቄው በቀጣይነት ይበልጥ እንዲጠናከር የግሉ ዘርፍ ተሳትፎና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ  ስኬታማ እንዲሆን የክልል ፕሬዝዳንቶችና የከተማ ከንቲባዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ይህም ከመሬት አቅርቦት፣ከመሰረተ ልማት አኳያ የሚገጥሙ ችግሮች እንዲፈቱ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡      

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው በቀጣዩ ወር የሚካሄደው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ እንደ አገር በአምራች ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።    


 

አምራቾችና ባለኃብቶች በኤክስፖው በመሳተፍ እድሉን በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡      

በዕለቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር  ዶክተር ዓለሙ ስሜ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መለያ /ሎጎ/ ይፋ አድርገዋል።   

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአገር አቀፍ ደረጃ ሚያዚያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ መደረጉ ይታወቃል። 

 

 

 

 

 

 

 

   

  

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

    

 

  

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም