የኢትዮጵያ አጭር፣ መካከለኛ፣ 3ሺህ ሜትር መሰናክል፣ እርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አጭር፣ መካከለኛ፣ 3ሺህ ሜትር መሰናክል፣ እርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጀመረ

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2015 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የአጭር፣ መካከለኛ፣ 3ሺህ ሜትር መሰናክል፣ እርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ ለአትሌቶች የውድድር እድል መፍጠር እንዲሁም የክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦችና ተቋማት አትሌቶች አቋማቸውን እንዲለኩ ማድረግ የሻምፒዮናው አላማ ነው ብለዋል።
በውድድሩ ላይ ከ19 ክለቦች እና ተቋማት የተወጣጡ ከ600 በላይ አትሌቶች ተሳታፊ መሆኑን ገልጸዋል።
በሻምፒዮናው መክፈቻ ላይ በሴቶች 3ሺህ ሜትር መሰናክል፣ በሴቶች ርዝመት ዝላይ እና በወንዶች ዲስከስ ውርወራ የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል።
ከፍጻሜ ውድድሮቹ በተጨማሪ ሌሎች የማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ።
ሻምፒዮናው እስከ መጋቢት 17 ቀን 2015 ዓ.ም ይቆያል።
የኢትዮጵያ አጭር፣ መካከለኛ፣ 3ሺህ ሜትር መሰናክል፣ እርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሁለት አስርት ዓመታትን እድሜ በላይ ማስቆጠሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።