ለኘሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባበር ስኬታማነት እንግሊዝ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ተገለፀ

358

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2015(ኢዜአ):-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የእንግሊዝ የልማት እና አፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር አንድሪው ሚሸልን በፅህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

በውይይቱ ኢትዮጵያና እንግሊዝ በልማት ትብብር ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ወዳጅነት እንዳላቸው ያስታወሱት አቶ ደመቀ ይህ ግንኙነት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ይበልጥ ሊሰሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተፈፃሚ በማድረግ ረገድ እየተተገበሩ ስላሉ እርምጃዎች ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ፤ የስምምነቱ የእስከ አሁን ሂደት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተናግረዋል።

በግጭቱ ወንጀል በመፈፀም የሚጠረጠሩ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግም የሽግግር ፍትህ ስርዓት ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

እንግሊዝ ለኢትዮጵያ እያደረገች ላለው የሰብዓዊ ድጋፍ አቶ ደመቀ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ይህ ተግባር በአሁኑ ወቅት በጦርነት እና በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በእንግሊዝ የፓርላማ አባል የሆኑትና የአገሪቱ የልማትና የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር አንድሪው ሚሸል በበኩላቸው በኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን በመንግስት በኩል የተወሰደውን እርምጃ እና የታየውን ቁርጠኝነት አገራቸው እንደምታደንቅ የገለፁ ሲሆን ለስኬታማነቱም እንግሊዝ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት ከድርቅና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ያጋጠማትን ፈተና እንግሊዝ እንደምትገነዘብ ገልጸው ለዚህ የሚሆን ድጋፍ ከረድኤት ድርጅቶችና ከሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን እንደሚደረግ ገልፀዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ እና እንግሊዝ በሁለትዮሽ እና በሌሎች የትብብር መስኮችም ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም