በአፍሪካ ዜጎችን ከድህነት ለማላቀቅ አካታች የምጣኔ ሀብት ስርዓትን መገንባት ይገባል

341

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12 / 2015 ዓ/ም (ኢዜአ) በአፍሪካ  በድህነት ላይ የሚገኙና ከልማት የተገለሉ ዜጎችን ህይወት በዘላቂነት ለማሻሻል አካታች የምጣኔ ሀብት ስርዓትን መገንባት እንደሚገባ የአፍሪካ የፋይናንስ፣ ምጣኔ ሀብት ልማትና ፕላን ሚኒስትሮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ገለጹ። 

ላለፉት አምስት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሔድ የነበረው 55ኛው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የፋይናንስ፣ ምጣኔ ሀብት ልማትና ፕላን ሚኒስትሮች ጉባኤ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ በማሳለፍ ዛሬ ተጠናቅቋል።

ኢትዮጵያ የአገር በቀል ምጣኔ ሃብት ማሻሻያና የእስካሁን ተሞክሮዋን በጉባኤው ላይ አቅርባለች።

አፍሪካ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀምና በአገራት መካከል ትብብርን በማጠናከር ህዝቧን ከድህነት ለማውጣት መስራት አንደኛው የጉባኤው ትኩረት ነበር።

የዘርፉ ሙያተኞ ኢ-ፍትሐዊነትና ድህነት ቅነሳ፣ ቀጣናዊ ትስስር፣ ኮቪድ-19፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ዓለም አቀፍ ክስተቶች በአፍሪካ ምጣኔ ሀብት ላይ ያደረሱት ተጽእኖ ላይ ውይይት አድርገዋል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የሚኒስትሮች ውይይት ደግሞ በአህጉር ደረጃ ድህነትን ለመቀነስ እና ብልጽግናን ለማረጋገጥ በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክቶ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ሊቀመንበር  እንዲሁም የኡጋንዳ የፋይናንስ፣ ኢኮኖሚና ልማት ሚኒስትር ሔነሪ ሙሳሲዚ  ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።


 

በመግለጫቸውም በጉባኤው የአፍሪካን ልማት ለማፋጠን በትብብር መስራት እንደሚገባ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን፣ ተጽዕኖ የሚቋቋም ምጣኔ ሀብት መገንባት፣ የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋት፣ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ፣ መሰረተ ልማት ላይ ሙዓለ ንዋይ ማፍሰስ ላይ በትኩረት ለመስራት አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል።

ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ማስፋት፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር፣ ለዲጂታል መሰረተ ልማት ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ጉባኤው ውሳኔ ማሳለፉን ነው ያነሱት።

በአፍሪካ ድህነትና ኢ-ፍትሐዊነትን መቀነስ ለመቀነስ አካታች ምጣኔ ሃብትን በመገንባት የዜጎችን ህይወት በዘላቂነት ማሻሻል ላይ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ፔድሮ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ሰፊ የስራ እድል ሊፈጥሩና ገንዘብ ሊያመነጩ የሚችሉ ዘርፎችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ  ገልጸዋል።

በአህጉሪቱ ያለው እምቅ የሰው ሃይል፣ የማዕድንና የደን ሀብት ዘላቂ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ለማሳካት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰው፤ ለስኬቱ በቅንጅት መስራት ለነገ የሚተው አይደለም ብለዋል። 

ተጠባባቂ ዋና ፀሐፊው አክለውም የተባበሩት መንግስታት በአፍሪካ መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማምጣት ቀጣናዊ ትስስርን፣ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ ማፋጠንን ጨምሮ ሌሎች  መርሃ ግብሮችን በመደገፍ አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅሰዋል።

ጉባኤው በሙያተኞች የቀረቡ ምክረ ሀሳቦችን እና በሚኒስትሮች የቀረቡ የአቋም መግለጫዎችን አጽድቋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም