ለፌዴራሊዝም ስርአት ግንባታ ሂደት መሳካት የዜጎችን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው

263

 አዲስ አበባ መጋቢት 12/2015(ኢዜአ)፦ ለፌዴራሊዝም ስርአት ግንባታ ሂደት መሳካት የዜጎችን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የህገ መንግስትና ፌደራሊዚም አስተምህሮ ማዕከል ገለጸ።

በህገ- መንግስትና የፌደራሊዝም አስተምህሮ ላይ በማተኮር ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በቢሾፍቱ ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው።

የስልጠና መርሃ ግብሩ ሲጀመር ንግግር ያደረጉት የህገ- መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል  ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሀይለየሱስ ታዬ፤ የፌዴራሊዝም ስርአትን በተመለከተ የግንዛቤ መፍጠር ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ስልጠና ከተለያዩ ተቋማት ለተውጣጡ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠና መጀመሩን ተናግረዋል።

የፌደራሊዝም ስርአት ብዝሃነትን በአንድ ላይ አጣምሮ የሚይዝ በመሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ሰፊ ግዛትና ብዝሃነት ላለባቸው አገራት አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል።

በመሆኑም ዜጎች የፌዴራሊዝም ስርአትን ጽንሰ ሃሳብና አስፈላጊነት በቅጡ እንድረዱ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።


 

በማእከሉ የህገ መንግስትና ፌደራሊዝም አሰልጣኝ ዘውዴ ደምሴ፤ ኢትየጵያዊያን የፌዴራሊዝም ስርአትን ጽንሰ ሃሳብና አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግስታት ስር ተመዝግበው ካሉ 192 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ 28 ሀገሮች ፌደራላዊ ስርዓትን የሚከተሉ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም