ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን እየተወጣን ነው---በምዕራብ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች

112

መተማ  መጋቢት 12/2015 (ኢዜአ) ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ወንጀለኞችን በማጋለጥ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን በምዕራብ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

በዞኑ ባለፉት ስምንት ወራት በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተሳትፈው የተገኙ 49 ግለሰቦች በጽኑ እስራት እንደተቀጡም የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል።

የመተማ ዮሐንስ ከተማ ነዋሪ ሼክ ሲራጅ አህመድ እንዳሉት ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እየተወጡ ናቸው።

ለዚህም ባለፈው የካቲት ወር 2015 ዓ.ም በርካታ ወጣቶች በህገወጥ መንገድ ወደሱዳን ሊሻገሩ ሲሉ ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በማድረስ ህይወታቸውን መታደጋቸውን ገልጸዋል።

ለዜጎች ሞትና እንግልት ምክንያት የሆነውን ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል ወንጀለኞችን ለጸጥታ አካላት አጋልጦ በመስጠት የጀመሩትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች መምሪያ ኃላፊ ሊቀ ስዩማን ገብረስላሴ ሀይለማርያም በበኩላቸው በሰዎች ላይ መነገድ በፈጣሪም ይቅር የማያሰኝ ክፉ ሥራ መሆኑን ለህብረተሰቡ ትምህርት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ምዕመናን በዚህ ተግባር እንዳይሳተፉ ከመምከርና ከመገሰፅ በተጨማሪ የህገወጥ ዝውውሩ ተሳታፊዎችን ለሚመለከተው አካል በመጠቆም ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ የማስገንዘብ ሥራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በበኩሉ ባለፉት ስምንት ወራት በምዕራብ ጎንደር ዞን በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተሳትፈው ጥፋተኛ የተባሉ 49 ግለሰቦች በጽኑ እስራት መቀጣታቸውን አስታውቋል።

የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የወንጀል ጉዳዮች አገልግሎት አሰጣጥ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተገን ማማሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ዞኑ ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የሚሻገሩበት ነው።


 

በመሆኑም ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ባለፉት ስምንት ወራት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በቅንጀት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። 

"በእዚህም በህገ ወጥ መንገድ ድንበር በማሻገርና በሰዎች መነገድ ወንጀል የተሳተፉ ግለሰቦችን ለህግ በማቅረብ በኩል የተሻለ ሥራ ተሰርቷል" ብለዋል።

በወንጀሉ የተጠረጠሩ 59 ግለሰቦችም በ34 መዝገቦች ክስ ተመስርቶባቸው በፍርድ ቤቱ የማጣራት ሥራ ሲሰራ መቆየቱን አመልክተዋል።

ከቀረቡት የክስ መዝገቦች ውስጥ በ6 መዝገቦች የተከሰሱ 10 ተጠርጣሪዎች በነፃ ሲሰናበቱ በቀረበ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ጥፋተኝነታቸው የተረጋገጠ 49 ተከሳሾች በጽኑ እስራትና ገንዘብ እንዲቀጡ መደረጉን አቶ ተገን ተናግረዋል።

ግለሰቦቹ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀፅ 3 መሰረት ከ1 እስከ 7 ዓመት ከ3 ወር በሚደርስ ጽኑ እስራት መቀጣታቸውንም አመልክተዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ ወንጀሉን በመከላከልም ሆነ ወንጀለኞች እንዲቀጡ በማድረግ በኩል የህብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላ እንደነበር ጠቅሰው፤ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።


 

በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሚኒኬሽንና ሚዲያ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ወርቄ ጫኔ እንዳሉት፣ ዜጎችን በህገ ወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ ግለሰቦችን በመያዝ በህግ እንዲጠየቁ እየተደረገ ነው።

"ከዚህ ጎን ለጎን ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ ሲሂዱ የሚደርስባቸውን ሰብዓዊ፣ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቃት አስቀድሞ ለመከላከል የህዝቡን ግንዛቤ በማሳደግ የመከላከሉን ስራ እንዲተባበሩ እየተደረገ ነው።" ብለዋል 

ምክትል ኮማንደሯ እንዳሉት መነሻቸውን ጎንደር አድርገው በዞኑ ቋራ፣ መተማና ምዕራብ አርማጭሆ በኩል ወደሱዳን ለመሻገር የሚሞክሩ ዜጎች በርካታ ናቸው።

በተያዘው በጀት ዓመት 693 ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ ሊሻገሩ ሲሉ ተይዘው ወደመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ መደረጉን ጠቁመው፣ ከፍተኛ የስነ ልቦና እና አካላዊ ጉዳት የሚደርስባቸው እንዳሉም ገልጸዋል።

ቁጥጥር በሚደረግባቸው ኬላዎች ህገወጥ መታወቂያ አሰርቶ ለማለፍ የሚሞከርበት ሁኔታ መኖሩንም ምክትል ኮማንደር ወርቄ ጠቁመዋል።

በዞኑ የተዘዋዋሪዎች ማቆያ አለመኖሩ በፀጥታ አካሉና በተዘዋዋሪዎች ላይ ጫና መፍጠሩን ጠቁመው፣ ይህም በተለይም ለምስክርነት እንዲቆዩ የሚደረጉ ተዘዋዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም