በአማራ እና ጋምቤላ ክልሎች በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ ያለው የመሬት ኢንቨስትመንት አስተዳደር ስርዓት ስኬታማ ሆኗል--የግብርና ሚንስቴር

220

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2015 (ኢዜአ) በአማራ እና ጋምቤላ ክልሎች በሙከራ እየተተገበረ ያለው የመሬት ኢንቨስትመንት አስተዳደር ስርዓት ስኬታማ መሆኑን የግብርና ሚንስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ ገለጹ።

"ኃላፊነት የተሞላበት የመሬት አስተዳደር የአካታችና ዘላቂ ልማት ጎዳና" በሚል መሪ-ሀሳብ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ፤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የመሬት አስተዳደር ስርዓቱ ለኢንቨስትመንት የሚውል መሬትን ከመለየትና በስርዓት ከመጠቀም አኳያ ዘርፈ ብዙ ችግር አለበት።

መንግሥት ችግሩን ለማቃለል መሪ እቅድ አዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በዚህም በጀርመን ተራድኦ ድርጅት/.አይ.ዜድድጋፍ በአማራ እና ጋምቤላ ክልሎች እየተተገበረ ያለው የኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር የሙከራ ፕሮጀክት የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት እያገዘ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በሙከራ ደረጃ ስኬታማ በመሆኑ የተገኙ ጥንካሬዎችን በመቀመር በሌሎች አካባቢዎችም ለማስፋፋት እንደሚሰራ ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያረጋገጡት።


 

የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ በበኩላቸው፤ በመሬት ኢንቨስትመንት ላይ ያሉ ክፍተቶችን በየወቅቱ የመፈተሽና የመገምገም ስራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

በዚህም በግምገማው የተለዩ ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችል መሬትን ታሳቢ ያደረገ የሶስት ዓመት የኢንቨስትመንት እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን በመጠቆም።

አብዛኛው የኢንቨስትመንት መስኮች መሬትን መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።


 

በጀርመን ተራድኦ ድርጅት/.አይ. ዜድ/ የፕሮጀክቱ ኃላፊ ክርስቲያን ሜስመርም፤ መሬት ውስንና ታዳሽ ያልሆነ ሃብት በመሆኑ በዘርፉ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል።

በተለይ በመሬት አሰጣጥ ሂደት የጥበቃ እና የምክክር ስልቶች ባለመኖራቸው የመሬት መራቆት፣ ውዝግብ እና መፈናቀልን ሊፈጥሩ ይችላሉ ነው ያሉት።

በመሆኑም ፕሮጀክቱ በዘርፉ ያለውን ክፍተት በመለየት በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ እና ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በፕሮጀክቱ አማካይነት ለኢንቨስትመንት የሚውል የመሬት አስተዳደር ሶፍትዌር ማልማትን ጨምሮ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ከጋምቤላና ከአማራ ክልል የመጡ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

በዚህም በባለሃብቶችና በማህበረሰቡ የመሬት አጠቃቀም ዙሪያ የነበሩ ያለመናበብ ችግሮችን በማቃለል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም