የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቆጮን በዘመናዊ መንገድ ማቀነባበር የሚያስችል ቴክኖሎጂን ለህብረተሰቡ ለማድረስ እየሰራ ነው

224

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2015(ኢዜአ) የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቆጮን በዘመናዊ መንገድ ማቀነባበር የሚያስችል ቴክኖሎጂን በስፋት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ።

በዩንቨርሲቲው የእንሰት ፕሮጀክት ተመራማሪና አስተባባሪ ዶክተር አዲሱ ፈቃዱ እንሰት በባህላዊ መንገድ ሲዘጋጅ ብዙ ተግዳሮቶች ያሉበት፣ የመብላላት ሂደቱ ረጅም ጊዜ የሚፈጅና ከፍተኛ ጉልበት የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም በቀላሉ እንሰትን መፋቅ የሚያስችል ማሽን በመስራት የቆጮውን ጥራት ከመጠበቅ ባለፈ የእናቶችን ድካም ማስቀረት የሚያሰችል ቴክኖሎጂ መፍጠሩን ገልጸዋል።


 

አዲሱ ቴክኖሎጂ ብክነትን ከመቀነስ ባሻገር አርሶ አደሩ ድረስ በመሞከረና ውጤታማነቱን በማረጋገጥ አርሶ አደሩ ጥቅም ላይ እንዲያውል መደረጉን ክተ አዲሱ አብራርተዋል፡፡

እንሰት ምግብነት ባሻገር የተለያዩ አይነት ምግቦችን ማምረት የሚያስችል ጥራቱን የጠበቀ ዱቄት በማዘጋጀት ኩኪስ፣ ኬክና ዳቦ የመሳሰሉትን ማምረት እንደሚቻል ለህረተሰቡ የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱ ተጠቁሟል።


 

በዚህም ወጣቶች ተደራጅተው ዱቄቱን በማምረት እንዲሸጡ በማድረግ የስራ እድል መፍጠር መቻሉ ተገልጿል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የሰራቸው እነዚህ የእንስት መፋቂያ አውቶማቲክ ማሽን፣ የእንሰት ማብለያ ማሽን እንዲሁም በሞተር የሚሰራ የአሚቾ(የእንሰት የታችኛው ክፍል) መፍጫ ማሽን የፈጠራ ስራዎች ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን እውቅና እንዳገኙም ተገልጿል፡፡


 

በቴክኖሎጂው ተጠቃሚ የሆኑ ሴት አርሶ አደሮች በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ያመጣውን ዘመናዊ ማሽን መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ድካም እንደቀነሰላቸውና ምርቱም ተፈላጊ ሆኖ ጥሩ ዋጋ እያወጣላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂን በማሻሻል በሰራቸው ስራዎች በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በርካታ እውቅናዎችን እንዳገኘ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም