ተቋማት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርትን ተግባራዊ በማድረግ ለካፒታል ገበያ ስርአት ሊዘጋጁ ይገባል-የካፒታል ገበያ ባለስልጣን

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2015(ኢዜአ) ተቋማት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርትን ተግባራዊ በማድረግ ለካፒታል ገበያ ስርአት ሊዘጋጁ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ ካፒታል በማሰባሰብ የገንዘብ ስርዓቱን በአዳዲስ ፈጠራዎች በመደገፍና የኢንቨስትመንት ስጋቶችን የመጋራት አሰራርን በማስፋፋት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ልማት የሚደግፍ የካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 ጸድቋል፡፡

በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን እውን ለማድረግ የሚያስችል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የተቋማት የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀት እንዲኖር ቀደም ብሎ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

የህዝብ ጥቅም ያለባቸው ተቋማትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ መንግስት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት የሚያቀርቡበት "የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ" አዋጅ ቁጥር 847/2006 ስራ ላይ ውሏል፡፡

በዚህም የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብን በኃላፊነት የሚመራና የሚቆጣጠር የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ገቢራዊ ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ሒክመት አብደላ በዚሁ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ቦርዱ እስከተቋቋመበት ጊዜ ድረስ የራሷም ሆነ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃ አልነበራትም ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓት ከሌላቸው 40 የዓለም ሀገራት አንዷ እንደነበረች አስታውሰዋል፡፡

ከለውጡ በኋላ ግን በሀገሪቱ ሊጀመር በታሰበው የካፒታል ገበያ ዘርፉ ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት በመደረጉ የሀገር ውስጥ ተቋማት የተወዳዳሪነት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ካሉት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተቋማት መካከል ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ማቅረብ የሚገደዱ ባንኮች፣ ኢንሹራንሶችና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሪፖርት ማቅረብ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ተቋማት በካፒታል ገበያ ከዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ጋር ተወዳዳሪና ተመራጭ ለመሆን ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብን ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀት እንዳለባቸው ጠቁመው ቦርዱም አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ የካፒታል ገበያን ማስጀመር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

ደንቦችና መመሪያዎችን ማዘጋጀትና በቂ ግንዛቤ መፍጠር፤ የሀገር ውስጥ ተቋማት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እንዲያሳድጉ ማገዝ የዝግጅቱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ አዲስ በሆነውና በቅርቡ ለምትጀምረው የካፒታል ገበያ ለመሳተፍ የሀገር ውሰጥ ተቋማት  "ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃ" ማሟላት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት የተቋማትን ተዓማኒነት ከማጉላቱም ባለፈ ባለሀብቶች የድርጅቶችን አቅም ማየትና መገምገም የሚችሉበት መተማመኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኦዲት ቦርዱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሒክመት አብደላ፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ሳያዘጋጅና ሳያቀርብ በካፒታል ገበያ ላይ የሚሳተፍ ተቋም በዓለም ላይ አለመኖሩን ተናግረዋል።

በመሆኑም ተቋማት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ሲያቀርቡ የውጭ ድርጅቶች ሪፖርቶችን አይተው በቀላሉ ስለሚረዱት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢንቨስት ለማድረግ ትኩረት ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃን ከሚከተሉ ሀገሮች ተርታ ለመቀላቀል መዘጋጀቷን ገልጸዋል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ፤ ተቋማት ያሉበትን ቁመና ማወቁ ለራሳቸው ጥቅም ጭምር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የኮርፖሬት ቦንድ ሽጦ ተጨማሪ ገንዘብ ገበያው ላይ ለመሰብሰብ ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት ሊኖረው ይገባል ብለዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ የሚሳተፉ ተቋማት እንዴት መስተናገድ እንዳለባቸው የሚገልጽ አሰራር እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የካፒታል ገበያ የኩባንያ ባለቤቶች፣ ለግለሰቦች ድርሻ በመሸጥ ገንዘብ የሚያሰባስቡበትና ከድረሻ ሽያጭ በተጨማሪ የብድር ሰነዶች የሚሸጡበት ዓለም አቀፍ የገበያ ስርአት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም