የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ አመራሩ ግንባር ቀደም ርብርቡን አጠናክሮ መቀጠል አለበት- ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ 

217

ድሬዳዋ መጋቢት 12/2015(ኢዜአ)፡- የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ከዳር በማድረስ የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ አመራሩ ግንባር ቀደም ርብርቡን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ።  

የብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ከፍተኛ አመራሮች በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያዩ ነው። 

በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ያለው ውይይት እየመሩ የሚገኙት ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፤ በሀገራችን የተጀመረው ሁሉን አቀፍ የብልጽግና ጉዞ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችና ድሎች እየተመዘገበበት ቢሆንም በርካታ ተግዳሮቶች እየተፈታተኑት ይገኛል ብለዋል።

ፈተናዎችን በማለፍ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በየደረጃው የሚገኘው የብልጽግና ፓርቲ አመራር ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን ከምንጊዜውም በላይ መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ከዲር ጁሃር በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር የገጠሙን ችግሮች ለመፍታት የፓርቲውን ተቋማዊ አቅም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ፓርቲው በየደረጃው የሚገኙ አባላቱንና ህዝቡን ከጎን በማሳለፍ የተጀመረውን የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞ ዳር ለማድረስ የተጀመረው ርብርብ አጠናክሮ መቀጠል ላይ በትኩረት መሰራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

ውይይቱ የተዘጋጀው በየደረጃው የሚገኘው አመራር ፈተናዎችን በድል ለመሻገር የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለማጠናከር መሆኑን የገለጹት የብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ናቸው።


 

የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ዳር ለማድረስ በቀጣይ ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር የተቀናጀ ርብርብ እንዲያጠናክር ይደረጋል ብለዋል።

ዛሬ የተጀመረውና እስከ ነገ በሚቀጥለው ውይይት ላይ በየደረጃው የሚገኙ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም