በጅግጅጋ ከተማ በ22 ሚሊዮን ብር ወጪ ለሚገነባ የምገባ ማዕከል የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

238

ጅግጅጋ መጋቢት 12/2015(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ትብብር በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በ22 ሚሊዮን ብር ወጪ ለሚገነባ የምገባ ማዕከል ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ። 

"የጅግጅጋ ከተማ ተስፋ ብርሀን አሙዲ" ለተሰኘው የምገባ ማዕከል የመሰረት ድንጋዩ በጋራ ያስቀመጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የሶማሌ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሀመድ ሻል እንዲሁም የጅግጅጋ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ ኢንጂነር ዚያድ አብዲ ናቸው። 

የጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ በወቅቱ ማዕከሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በቀን 2ሺህ ለሚሆኑ አቅመ ደካማና ህሙማን የምገባ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። 

በአምስት ሺህ ስኩየር ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባውን ማዕከል በሶስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ተናግረዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ 15 የምገባ ማዕከላት በቀን 30ሺህ ሰዎች የምገባ አገልግሎት እንደሚያገኙ አውስተዋል።

ይህንን ተሞክሮ ወደ ክልሉ በማምጣት ተግባራዊ እንዲሆን ለማገዝ ይሰራል ብለዋል። 

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የፕሮጅክት አስተዳዳር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጉሌድ አሊ፤ በጅግጅጋ  ከተማ አቅመ ደካማ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መመገቢያ ማዕከል ለመገንባት እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም