በአፍሪካ የግብርና ምርታማነትን  ማሳደግና የዲጂታል መሰረተ-ልማትን  ማጠናከር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል

277

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12 / 2015 ዓ/ም (ኢዜአ) በአፍሪካ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግና የዲጂታል መሰረተ-ልማትን በማጠናከር ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑ ተገለጸ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ለአፍሪካ ዘላቂ ልማትና እድገት ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጧል።

በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የተካሄደው 55ኛው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የፋይናንስ፣ ምጣኔ ኃብት ልማትና ፕላን ሚኒስትሮች ጉባዔ በዓለም አቀፍና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሳኔ በማሳለፍ ተጠናቋል።

በጉባዔው በዋነኝነት የድህነት ቅነሳ፣ ቀጣናዊ ትስስር፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ በማተኮር ተወያይቶ መፍትሔዎችንም አስቀምጧል።

አፍሪካ የተፈጥሮ ኃብቷን በመጠቀም ከድህነት መውጣት የምትችልባቸውን አማራጮች፣ አህጉራዊ ትብብሮችና ነፃ የንግድ ቀጣናን ማጠናከር በዓይነተኛ መፍትሔነት ተነስተዋል።

በአፍሪካ በስፋት የሚስተዋለውን ድህነትና አጠቃላይ የልማት መሰናክሎችን ለማስወገድ የአገራት ትብብርና አብሮ መሥራት ለነገ የማይባል ተግባር መሆን እንዳለበትም በጉባዔው ተመላክቷል።

በመሆኑም በሙያተኞች የቀረቡ ምክረ-ሃሳቦችንና በሚኒስትሮች የቀረቡ አስተያየቶችን በማጠናከር የአቋም መግለጫ በማውጣት ጉባዔው ተጠናቋል።

የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን፣ በተጽዕኖዎች የማይናወጥ ምጣኔ ኃብት መገንባት፣ የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋት፣ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግና መሰረተ-ልማት ላይ መዋዕለ-ንዋይ ማፍሰስ የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች እንዲሆኑ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

በተመሳሳይ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስፋትና አጠናክሮ መቀጠል፤ አህጉራዊና ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል።

በአፍሪካ የዲጂታል መሰረተ-ልማት ግንባታ ላይ በስፋት ኢንቨስት ማድረግ በቀጣይ ዋነኛ የትኩረት መስክ ተደርጎ የሚሰራበት መሆኑም ተነስቷል።

በአፍሪካ ድህነትና ኢ-ፍትሃዊነትን ለመቀነስ አገራት የሚቀርጿቸው ፖሊሲዎች አካታች መሆን እንዳለባቸውም ተመላክቷል።

በአፍሪካ የምጣኔ ኃብት እድገት ለማስመዝገብ በቀጣናዊ ትስስር፣ ነፃ የንግድ ቀጣና እና ሌሎች  መርሃ- ግብሮችን በመደገፍ አጋርነቱን የሚቀጥል መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት አረጋግጧል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተጠባባቂ  ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ፤ በጉባዔው ማጠናቀቂያ ላይ ባደረጉት ንግግር የመንግሥታቱ ድርጅት ለአፍሪካ ዘላቂ ልማትና እድገት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም