ፈተናዎችን ለመሻገር አመራሩ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን ሊያጎለብት ይገባል - አቶ ተስፋዬ ይገዙ

ሚዛን አማን መጋቢት 12/2015 (ኢዜአ)፡- ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን ለመሻገር አመራሩ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን ሊያጎለብት እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ተስፋዬ ይገዙ አሳሰቡ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ነው።

ውይይቱን እየመሩ የሚገኙት የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ተስፋዬ ይገዙ ናቸው።


 

አቶ ተስፋዬ እንዳሉት ውይይቱ አመራሩ በለውጡ ውስጥ የተገኙ ስኬቶችን ተገንዝቦ እያጋጠሙ ያሉ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶችን ለማለፍ ግንባር ቀደም ሚናውን እንዲወጣ ለማጠናከር ነው።

አመራሩ ችግሮችን በመረዳት የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በመፍጠር ፈተናዎችን መሻገር የሚያስችል ተግባር እንዲፈጽም ለማመቻቸት የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።

የውይይት መድረኩ "ድሎችን በማጽናትና ፈተናዎችን የመሻገር ወቅታዊና ታሪካዊ የአመራር ተልዕኮ" የሚል ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።

እስከ ነገ በሚቀጥለው ውይይት ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳን ጨምሮ ሌሎች  አመራሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም