ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነቱን እየተገበረች በምትገኝበት ወቅት በአሜሪካ መንግስት የታየው ከፋፋይና ሚዛናዊ ያልሆነ አካሄድ ለአካታች የሰላም ውይይቱ እንቅፋት የሚሆን ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

193

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነቱን እየተገበረች በምትገኝበት ወቅት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የታየው ከፋፋይና ሚዛናዊ ያልሆነ አካሄድ ኢትዮጵያ ለምታደርገው አካታች የሰላም ውይይት እንቅፋት አንደሚሆን የኢፌዴሬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የወጣውን የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚመለከት ሪፖርት አግባብነት እንደሌለው አስታውቋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጉዳዩን በተመለከተ ያወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር በጋራ ካደረጉት ምርመራ አንፃር ሲታይ ምንም አዲስ ግኝት ያልተካተተበት መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣውን ሪፖርት እንደማይቀበለው ገልጿል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያወጣው መግለጫ አንድን ወገን ብቻ መወንጀል ላይ ያነጣጠረ መሆኑንም ነው ሚኒስቴሩ በመግለጫው የጠቆመው።

በሌላ በኩል ሪፖርቱ ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጮችን ለመለየት ስራዎችን እየሰራች ባለችበት፤ ብሔራዊ ምክክር ለመጀመር በተዘጋጀችበት ወቅት ላይ የወጣ በመሆኑ ወቅቱን ያልጠበቀ መሆኑንም ገልጿል።

በተጨማሪም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የወጣው ሪፖርት ዓላማ ምንም ይሁን ምን በሀገሪቱ አንድን ወገን በሌላኛው ላይ የማነሣሣት ይዘት ያለው ሆኖ ማግኘቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አመላክቷል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በአሜሪካ መንግስት የወጣው ሪፖርት ሀገሪቱ አካታች የሰላም ሂደት እንዲረጋገጥ ስታደርገው የቆየችውን ድጋፍ የሚያጨናግፍ ነው ብሏል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት እንደሚያጠናክር ተስፋን የፈነጠቀ ነው ያለው መግለጫው፤ በጉብኝቱ ወቅት የተደረገው ግልጽ ውይይት እና የተደረሰበት መግባባት የሁለቱን ሀገራት ስትራቴጂያዊ አጋርነት ለማስቀጠል ይረዳል ብላ ኢትዮጵያ እንደምታምን ገልጿል።

በሽግግር ፍትሕ እና ሀገራዊ ምክክር በማካሄድ መግባባት መፍጠርን ጨምሮ ለተበዳዮች ፍትሕን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የተጠያቂነት እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ያረጋገጠው መግለጫው፤ የኢትዮጵያ ወዳጆችም ገንቢ ድጋፍ በመለገስ ይህን ሂደት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም