በድሬዳዋ በመንግስት ተቋማት የተጀመረው የለውጥ ሥራ ፈጣን አገልግሎት ማግኘት አስችሎናል--ተገልጋዮች

121

ድሬዳዋ መጋቢት 12/2015(ኢዜአ)- በድሬዳዋ አስተዳደር በመንግስት ተቋማት የተጀመረው የለውጥ" ሥራ ፈጣን አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻላቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተገልጋዮች ተናገሩ።

መንግስታዊ ተቋማት የተጀመረውን የሪፎርም ሥራን በማጠናከር የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአስተዳደሩ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አስታውቋል።

የለውጥ ሥራው በተጀመረባቸው ተቋማት የተገለገሉ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በተቋማቱ  እየተካሄደ ያለው ለውጥ የሚፈልጉትን አገልግሎት በፍጥነት ለማግኘት አስችሏቸዋል። 

መንግስት የነዋሪዎችን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በተቋማቱ የጀመራቸውን ስራዎች  ማጠናከር እንደሚገባ  አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል።

በአስተዳደሩ የገቢዎች ባለስልጣን መሥሪያ ቤት አገልግሎት ለማግኘት የተገኙትና በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ተካ ኒኮላ በተቋሙ የተዘረጋው ዘመናዊ አሠራርና የሠራተኞቹ መስተንግዶ የሚፈልጉትን አገልግሎት በደቂቃዎች ውስጥ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል

በተለይ ለነጋዴው ማህበረሰብ ፈጣን አገልግሎት ማግኘት ማለት ይባክን የነበረውን ጊዜና ጉልበት ለስራ በማዋል ተጨማሪ ሃብት ለማግኘትና የአስተዳደሩን ገቢ ለማሳደግ እንደሚያግዝ አስተያየት ሰጥተዋል።

አገልግሎቱ ወደ ሌሎች ተቋማትም መስፋፋት ይገባዋል ብለዋል።


 

በአስተዳደሩ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ  ለአገልግሎት የመጡት አቶ አሰፋ ይርጋ በቢሮው የንግድ ጽህፈት ቤት የተጀመረው የአሰራር ለውጥ አገልግሎት የማግኘት ጥያቄያቸውን የመለሰ መሆኑን ገልጸዋል

በተቋሙ የተዘረጋው "ኦን ላይንአገልግሎት አሰጣጥ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለማግኘት ስለሚያግዝ ያስደስታል ብለዋል።


 

በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የመንግስት አገልግሎት ለማግኘት የተገኙት አቶ ሐሰን አህመድ፤ የመጡበትን  የመሬት ጉዳይ  በትህትናና በፍጥነት መስተንግዶ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ተቋም አገልግሎት ለማግኘት የመጡት አቶ ረሻድ መሐመድ፤ በተቋሙ ለነባር የይዞታ ማረጋገጫ  ጥያቄ በተገቢው መንገድ እየተመለሰ መምጣቱን መረዳት እንደቻሉ  ተናግረዋል።


 

በአስተዳደሩ የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ  የሪፎርም ትግበራ ጥናት ድጋፍና ክትትል ዳይሬክተር አቶ  ዘለቀ አባተ፤ በበጀት ዓመቱ ውስጥ በአስተዳደሩ በዘጠኝ ተቋማትና በሶስት የከተማ ቀበሌዎች የተጀመረው የለውጥ አሰራር የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እያስቻለ መሆኑን አስረድተዋል።


 

በተቋማቱ በጅምር ደረጃ የሚታየውን ለውጥ ለማጠናከር በሂደቱ የታዩ ክፍተቶችን ከማረም ጎን ለጎን ለውጡን በሌሎች ተቋማት ለማስጀመር  እንደሚሰራም ገልጸዋል።

የለውጥ ሥራው ከተጀመረባቸው ተቋማት መካከል የአስተዳደሩ የገቢዎች ባለስልጣን፣ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ፣  የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ፣ ጤና ቢሮ፣ የፍትሕ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ፣ የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮና የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ  እንደሚገኙበት ተጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም